ዘፍጥረት 11:27-32
ዘፍጥረት 11:27-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አራንም ሎጥን ወለደ። አራንም በተወለደባት ሀገር በከለዳውያን ምድር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮርም ሚስት የአራን ልጅ ሚልካ ናት፤ አራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው። ሦራም መካን ነበረች፤ ልጆችም አልነበሩአትም። ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የአራንን ልጅ ሎጥን፥ የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ምድር አወጣቸው። ወደ ካራንም መጡ፤ በዚያም ተቀመጡ። ታራም በካራን ምድር የኖረበት ዘመን ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።
ዘፍጥረት 11:27-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የታራ ትውልድ ይህ ነው፦ ታራ፣ አብራምን ናኮርንና ሐራንን ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ። ሐራን፣ አባቱ ታራ ገና በሕይወት እንዳለ በከለዳውያን ምድር በምትገኘው በተወለደባት ከተማ በዑር ሞተ። አብራምና ናኮር ሁለቱም ሚስት አገቡ፤ የአብራም ሚስት ሦራ ስትባል፣ የናኮር ሚስት ደግሞ ሚልካ ትባል ነበር፤ ሚልካም የሐራን ልጅ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነበረ። ሦራ መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም። ታራ ልጁን አብራምን፣ ሐራን የወለደውን የልጅ ልጁን ሎጥን እንዲሁም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነዓን ለመሄድ በከለዳውያን ምድር ከምትገኘው ከዑር አብረው ወጡ፤ ነገር ግን ካራን በደረሱ ጊዜ በዚያ ተቀመጡ። ታራ 205 ዓመት ኖሮ በካራን ሞተ።
ዘፍጥረት 11:27-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራም አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ። ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዩስካ አባት ነው። ሦራም መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም። ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፤ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ። የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።
ዘፍጥረት 11:27-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአብራም፥ የናኮርና የሃራን አባት የነበረው የታራ ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፤ ሃራን ሎጥን ወለደ፤ ሃራን አባቱ ታራ ገና በሕይወት ሳለ በተወለደባት ከተማ በኡር ሞተ፤ ኡር የምትገኘው በከለዳውያን ምድር ነበር። አብራም ሣራይን አገባ፤ ናኮር ደግሞ ሚልካን አገባ፤ እርስዋም ዪስካንን የወለደ የሃራን ልጅ ናት። ሣራይ መኻን በመሆንዋ ልጅ አልወለደችም ነበር። ታራ ልጁን አብራምን፥ ከሃራን የተወለደውን የልጅ ልጁን ሎጥን፥ የአብራም ሚስት የሆነችውን ምራቱን ሣራይን ይዞ በባቢሎን የምትገኘውን የኡርን ከተማ በመተው ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ተነሣ፤ ወደ ካራን ዘልቀው እዚያ ተቀመጡ። ታራ 205 ዓመት ሲሆነው በካራን ሞተ።
ዘፍጥረት 11:27-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፥ ሐራንም ሎጥን ወለደ። ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፥ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፥ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፥ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው። ሦራም መካን ነበረች፥ ልጅ አልነበራትም። ታራም ልጁን አብራምን፥ የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥንና የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሣራን ወሰደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፥ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ። የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፥ ታራም በካራን ሞተ።