ዘፍጥረት 1:1-13
ዘፍጥረት 1:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድር ግን ባዶ ነበረች፤ አትታይምም ነበር፤ የተዘጋጀችም አልነበረችም፤ ጨለማም በውኃው ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ይሰፍፍ ነበር። እግዚአብሔርም፥ “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ እግዚአብሔርም በብርሃኑና በጨለማው መካከል ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን “ቀን፥” ጨለማውንም “ሌሊት” ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ አንደኛ ቀንም ሆነ። እግዚአብሔርም፥ “በውኃው መካከል ጠፈር ይሁን፤ በውኃና በውኃ መካከልም ይለይ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትንም ውኆች ለየ። እግዚአብሔር ያን ጠፈር “ሰማይ” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ ሁለተኛም ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ከሰማይ በታች ያለው ውኃም በመጠራቀሚያው ተሰበሰበ፤ የብሱም ተገለጠ። እግዚአብሔርም የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፤ የውኃ መጠራቀሚያውንም “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም “ምድር በየዘሩ፥ በየወገኑና በየመልኩ ዘር የሚሰጥ ቡቃያን፥ በምድርም ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ ታብቅል” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ምድርም በየዘሩ፥ በየወገኑና በየመልኩ የሚዘራ ቡቃያን፥ በምድር ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ። ሦስተኛም ቀን ሆነ።
ዘፍጥረት 1:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች። የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር። እግዚአብሔርም “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ ብርሃኑን ከጨለማ ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን “ቀን”፣ ጨለማውን “ሌሊት” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን። እግዚአብሔር፣ “ውሃን ከውሃ የሚለይ ጠፈር በውሆች መካከል ይሁን” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ጠፈርን አድርጎ ከጠፈሩ በላይና ከጠፈሩ በታች ያለውን ውሃ ለየ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን። ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፤ ደረቁ ምድር ይገለጥ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር ደረቁን ምድር፣ “የብስ”፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔር፣ “ምድር ዕፀዋትንም፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በምድር ላይ ዘር ያዘሉ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። ምድር ዕፀዋትን፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በውስጣቸው ዘር ያለባቸው ፍሬ የሚያፈሩትን ዛፎች በየወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። መሸ፤ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን።
ዘፍጥረት 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ስማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች፤ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ስፍፎ ነበር። እግዚአብሔርም፤ ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራዉ። ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ አንድ ቀን። እግዚአብሔርም፤ በዉኖች መካከል ጠፈር ይሁን በዉኂ መካከል ይከፈል አለ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኖች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራዉ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፤ ሁሉተኚ ቀን። እግዚአብሔርም፤ ከሰማይ በታች ያለዉ ውኂ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፤ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራዉ የዉኂ መከማቻዉንም ባሕር አለዉ፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም፤ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድር ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ ሦስተኚ ቀን።
ዘፍጥረት 1:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። በዚያን ጊዜ ምድር ቅርጽ የሌላትና ባዶ ነበረች፤ ጨለማም በጥልቁ (ውቅያኖስ) ላይ ነበር፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃው ላይ ይሰፍ ነበር። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም፥ ብርሃን መልካም መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔርም ብርሃንን ከጨለማ ለየ። እግዚአብሔር ብርሃኑን “ቀን” ብሎ ጠራው፤ ጨለማውንም “ሌሊት” ብሎ ሰየመው። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ ይህም አንድ ቀን ሆነ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ውሃውን ከውሃ የሚለይ ጠፈር ይሁን” አለ፤ በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ጠፈርን ፈጠረ፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉት ውሆች ይለያዩ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ፥ ሌሊቱም ነጋ፤ ሁለተኛ ቀን ሆነ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “የብሱ ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ከሰማይ በታች ያለው ውሃ ሁሉ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፤ በአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ “ባሕር” ብሎ ሰየመው፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ምድር አትክልትን፥ የእህል አዝርዕትን፥ ፍሬ የሚያፈሩ የፍሬ ዛፎችንና ተክሎችን በየዐይነቱ ታብቅል” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። በዚህ ዐይነት ምድር አትክልትን፥ በየዐይነቱ የእህል አዝርዕትንና ዘር በውስጡ ያለውን ፍራፍሬ የሚያስገኙ ተክሎችን አበቀለች፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ ሦስተኛ ቀን ሆነ።
ዘፍጥረት 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ቅርጽ የሌላትና ባዶ ነበረች፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ “ብርሃን ይሁን” ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንደኛ ቀን። እግዚአብሔርም፦ “በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል” አለ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፥ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም፦ “ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፥ በአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ “ባሕር” አለው፥ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም፦ “ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድር ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል” አለ፥ እንዲሁም ሆነ። ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።