በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድር ግን ባዶ ነበረች፤ አትታይምም ነበር፤ የተዘጋጀችም አልነበረችም፤ ጨለማም በውኃው ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ይሰፍፍ ነበር። እግዚአብሔርም፥ “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ እግዚአብሔርም በብርሃኑና በጨለማው መካከል ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን “ቀን፥” ጨለማውንም “ሌሊት” ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ አንደኛ ቀንም ሆነ። እግዚአብሔርም፥ “በውኃው መካከል ጠፈር ይሁን፤ በውኃና በውኃ መካከልም ይለይ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትንም ውኆች ለየ። እግዚአብሔር ያን ጠፈር “ሰማይ” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ ሁለተኛም ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ከሰማይ በታች ያለው ውኃም በመጠራቀሚያው ተሰበሰበ፤ የብሱም ተገለጠ። እግዚአብሔርም የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፤ የውኃ መጠራቀሚያውንም “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም “ምድር በየዘሩ፥ በየወገኑና በየመልኩ ዘር የሚሰጥ ቡቃያን፥ በምድርም ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ ታብቅል” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ምድርም በየዘሩ፥ በየወገኑና በየመልኩ የሚዘራ ቡቃያን፥ በምድር ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ። ሦስተኛም ቀን ሆነ።
ኦሪት ዘፍጥረት 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 1:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች