ዕዝራ 1:1-3
ዕዝራ 1:1-3 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በኤርምያስ አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ከተፈጸመ በኋላ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፤ ደግሞም በጽሕፈት እንዲህ አለ፦ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤትን እሠራለት ዘንድ እንዳስብ አደረገኝ፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤትን ይሥራ፤
ዕዝራ 1:1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያ ዓመት፣ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንድሠራለት አዝዞኛል። ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚገኝ ማንኛውም ሰው አምላኩ ከርሱ ጋራ ይሁን፤ በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና በዚያ ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሥራ።
ዕዝራ 1:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፤ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤
ዕዝራ 1:1-3 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት አስቀድሞ የተናገረውን የትንቢት ቃል የፋርስ ተወላጅ ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ፈጸመው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ራሱ ቂሮስን አነሣሥቶ ከዚህ የሚከተለውን ትእዛዝ በጽሑፍ በማወጅ በንጉሠ ነገሥት ግዛቱ ሁሉ እንዲነበብ አደረገ። የፋርስ ንጉሠ ነገሥትም በዐዋጅ የሰጠው ትእዛዝ እንዲህ የሚል ነበር፦ “የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ገዢ አድርጎኛል፤ እርሱም ቤተ መቅደስን በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌም እንድሠራለት አዞኛል። ከእናንተ መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነ ሁሉ፥ አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደሚገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሥራ።
ዕዝራ 1:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት፥ በኤርምያስ አፍ የተናገረው የጌታ ቃል እንዲፈጸም፥ ጌታ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፥ ይህም በመንግሥቱ ሁሉ በአዋጅና በጽሑፍ እንዲያስነግር ነው፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማያት አምላክ ጌታ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፥ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እንድሠራለት አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ ማንም በእናንተ ውስጥ የሚኖር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ የጌታ የእስራኤል አምላክን ቤት ይሥራ፥ እርሱም በኢየሩሳሌም ያለ አምላክ ነው፤