ሕዝቅኤል 14:1-8
ሕዝቅኤል 14:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን? ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ። በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’ “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ! “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ። ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 14:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች በልባቸው ጣዖቶቻቸውን አኑረዋል፤ የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ለእነርሱ መልስ ልመልስላቸውን? ስለዚህ ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ ቢመጣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። ይህም የእስራኤልን ወገኖች በዐሳባቸው ከእኔ እንደ ተለዩበት እንደ ልባቸውና እንደ ርኵሰታቸው ያስታቸው ዘንድ ነው።” ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሓ ግቡ፤ ከበደላችሁም ተመለሱ፤ ፊታችሁንም ከኀጢአታችሁ ሁሉ መልሱ። ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ። ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ፤ እንዲጠፋም አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 14:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን? ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ። በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’ “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ! “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ። ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 14:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፥ እኔስ ከእነርሱ ልጠየቅን? ስለዚህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ከእኔ ተለይተዋልና የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዝ ዘንድ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ ብለህ ንገራቸው። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ። ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፥ ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ ከሕዝቤም መካከል አጠፋዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 14:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእስራኤላውያን መሪዎች አንዳንዶቹ የእኔን ምክር ለመጠየቅ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ፤ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች ልባቸውን ለጣዖቶች ሰጥተዋል፤ በደላቸው በፊታቸው እንቅፋት እንዲሆንባቸው አድርገዋል፤ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የእኔን ፈቃድ መጠየቃቸው ተገቢ ነውን?” ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው፦ “ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ልባቸውን ለጣዖቶች የሰጡና የጣዖት አምልኮአቸው በፊታቸው ዕንቅፋት እንዲሆንባቸው ያደረጉ አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ወደ ነቢዩ የሚመጡ ከሆነ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቶች ብዛት ተገቢ መልስ እሰጣቸዋለሁ። ይህን የማደርገው እኔን ትተው ወደ ጣዖቶቻቸው በመሄድ ከእኔ ተለይተው የነበሩትን የእስራኤላውያንን ሁሉ ልብ ለመመለስ ነው። “ስለዚህ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጣዖቶቻችሁን ትታችሁ ንስሓ ግቡ! ከአጸያፊ ተግባራችሁም ሁሉ ተመለሱ!’ “ከእስራኤላውያን አንዱ ወይም በእነርሱ መካከል ከሚኖሩ ባዕዳን ሰዎች አንዱ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶችን በማምለክ ኃጢአት የሚሠራ ቢሆን፥ በደሉም በፊቱ ዕንቅፋት እንዲሆንበት ቢያደርግና እንደገና ደግሞ ምክር ለመጠየቅ ወደ ነቢያት የሚመጣ ከሆነ እኔ እግዚአብሔር ራሴ መልስ እሰጠዋለሁ! እኔም በእርሱ ላይ አተኲሬ መቀጣጫና መዘባበቻ አደርገዋለሁ ከሕዝቤ መካከል አስወግደዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።
ሕዝቅኤል 14:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አንዳንዶች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፥ ታዲያ እንዲጠይቁኝ ልፍቀድላቸው? ስለዚህ ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማንም ሰው ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ወደ ነቢዩም የሚመጣ፥ እኔ ጌታ እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። ይህም የእስራኤልን ቤት ለመያዝ ነው፤ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ምክንያት በልባቸው ከእኔ ተለይተዋልና፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመለሱ፥ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ፊታችሁን መልሱ። ማንም ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም የሚቀመጥ መጻተኛ፥ ራሱን ከእኔ የሚለይ፥ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ስለ እኔም ለመጠየቅ ወደ ነቢዩ የሚመጣ፥ እኔ ጌታ ራሴ እመልስለታለሁ፥ ፊቴን በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ፥ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።