ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች በልባቸው ጣዖቶቻቸውን አኑረዋል፤ የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ለእነርሱ መልስ ልመልስላቸውን? ስለዚህ ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ ቢመጣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። ይህም የእስራኤልን ወገኖች በዐሳባቸው ከእኔ እንደ ተለዩበት እንደ ልባቸውና እንደ ርኵሰታቸው ያስታቸው ዘንድ ነው።” ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሓ ግቡ፤ ከበደላችሁም ተመለሱ፤ ፊታችሁንም ከኀጢአታችሁ ሁሉ መልሱ። ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ። ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ፤ እንዲጠፋም አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ትንቢተ ሕዝቅኤል 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሕዝቅኤል 14:1-8
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች