ዘፀአት 34:4-8
ዘፀአት 34:4-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀረጸ፤ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላት በእጁ ወሰደ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። ጌታም በፊቱ አለፈ፥ “ስሜም ጌታ እግዚአብሔር፥ መሓሪ፥ ይቅር ባይ፥ ከመዓት የራቀ ምሕረቱ የበዛ ጻድቅ፥ ለብዙ ሺህ ጽድቅን የሚጠብቅ፥ ቸርነትን የሚያደርግ፥ አበሳንና መተላለፍን፥ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኀጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” ሲል አወጀ። ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጎነበሰና ለእግዚአብሔር ሰገደ፦
ዘፀአት 34:4-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርቦ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶችም በእጆቹ ያዘ። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ። እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ርኅሩኅ ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።” ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤
ዘፀአት 34:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጐ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረበ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፥ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ፦ እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ፦
ዘፀአት 34:4-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ሙሴ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ልክ እንደ ፊተኞቹ ቀረጸ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ተነሥቶ ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ጽላቶቹን ይዞ ወደ ሲና ተራራ ወጣ። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ከእርሱ ጋር በዚያ ቆመ፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ቅዱስ ስሙንም አስታወቀው። እግዚአብሔር በፊቱ ሲያልፍ እንዲህ ብሎ ዐወጀ፤ “እኔ እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሐሪ አምላክ ነኝ፤ እኔ ለቊጣ የዘገየሁ፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬና ታማኝነቴ የበዛ ነው፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬንም እስከ ብዙ ሺህ ትውልድ እጠብቃለሁ፤ በደልን መተላለፍንና ኃጢአትን ሁሉ ይቅር እላለሁ፤ ነገር ግን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ ስለ ወላጆቻቸው ኃጢአት ከመቅጣት አልገታም።” ሙሴም ወዲያውኑ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤
ዘፀአት 34:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጐ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጠረበ፤ በማግስቱም ማልዶ ጌታ እንዳዘዘው ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ይዞ ወደ ሲና ተራራ ወጣ። ጌታም በደመና ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የጌታንም ስም አወጀ። ጌታም በፊቱ አልፎ እንዲህ ብሎ አወጀ፦ “ጌታ፥ ጌታ፥ መሓሪ አምላክ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽ፥ ፅኑ ፍቅሩና እውነቱ የበዛ፥ ፅኑ ፍቅሩን እስከ ሺህ ትውልድ የሚጠብቅ፥ አበሳን፥ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በደለኛውን ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት በልጆችና በልጅ ልጆች ላይ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ የሚያመጣ አምላክ ነው።” ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተደፍቶ ሰገደ፦