ዘፀአት 33:7-23
ዘፀአት 33:7-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይጠባበቁ ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋራ እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር። ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ ሲያዩት ሁሉም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይሰግዱ ነበር። ሰው ከባልንጀራው ጋራ እንደሚነጋገር እግዚአብሔር ከሙሴ ጋራ ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፤ ከዚያም ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ ረዳቱ የነበረው ብላቴናው የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴ እግዚአብሔርን አለው፤ “ ‘እነዚህን ሕዝብ ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ ከእኔ ጋራ የምትልከው ማን እንደ ሆነ ግን አላሳወቅኸኝም፤ ‘አንተን በስም ዐውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለህ ነበር። በእኔ ደስ ተሠኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።” እግዚአብሔር “ሀልዎቴ ከአንተ ጋራ ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፤ “ሀልዎትህ ከእኛ ጋራ ካልሄደ ከዚህ አትስደደን። አንተ ከእኛ ጋራ ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?” እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “በአንተ ደስ ስላለኝና በስም ስለማውቅህ፣ የጠየቅኸውን ያንኑ አደርጋለሁ” አለው። ከዚያም ሙሴ “እባክህ፤ ክብርህን አሳየኝ” አለው። እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “መልካምነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ በፊትህም ስሜን እግዚአብሔርን ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ፤ ነገር ግን፣ ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም።” ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ፤ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ ከዚያም እጄን አነሣለሁ፤ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን መታየት የለበትም።”
ዘፀአት 33:7-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም ድንኳኑን ወስዶ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ “የምስክሩም ድንኳን” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወደአለው ወደ ድንኳኑ ይወጣ ነበር። ሙሴም ከሰፈር ውጭ ወደአለው ድንኳን በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ እየጠበቀ ይቆም ነበር፤ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ ዐምደ ደመና ይወርድ ነበር፤ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ዐምደ ደመናው በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር። እግዚአብሔርም፥ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን አገልጋዩ ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይወጣም ነበር። ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “እነሆ፥ አንተ፦ ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም ከሁሉ ይልቅ ዐወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ዐውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ ይህም ትልቅ ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ ተገለጥልኝ” አለው። እግዚአብሔርም፥ “እኔ በፊትህ እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ” አለው። እርሱም፥ “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። በምድርም ከአለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ ተለይተን እንከብር ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልሄድህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ በእውነት ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል?” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ይህን ያልኸኝን ነገር አደርግልሃለሁ፤ በፊቴ ሞገስን አግኝተሀልና ከሁሉ ይልቅ ዐውቄሃለሁና”አለው። እርሱም፥ “ክብርህን አሳየኝ” አለው። እግዚአብሔርም፥ “እኔ በክብሬ በፊትህ አልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ እጠራለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፤ የምምረውንም እምራለሁ” አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እነሆ፥ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዐለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም በአለፈ ጊዜ በአለቱ ስንጥቅ ውስጥ አኖርሃለሁ፤ እስከ አልፍም ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፤ በዚያ ጊዜ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን ለአንተ አይታይም።”
ዘፀአት 33:7-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ የመገናኛውም ድንኳን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። ሙሴም ወደ ድንኳኑ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፥ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር። እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ አንተ፦ ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ከእኔም ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም፦ በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት አለው። እግዚአብሔርም፦ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው። እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። እግዚአብሔርም፦ እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።
ዘፀአት 33:7-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል ሕዝብ በሰፈሩበት ቦታ ሁሉ ሙሴ ድንኳኑን ከሰፈሩ ራቅ ባለ ቦታ ይተክለው ነበር፤ እርሱም “ድንኳን” ተብሎ ተጠራ፤ እግዚአብሔርን መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ወደዚያ ይሄድ ነበር። ሙሴ ወደዚያ በሄደ ቊጥር ሕዝቡ በየድንኳናቸው ደጃፍ ቆመው ሙሴ ወደ ድንኳን እስኪገባ ድረስ ይመለከቱታል። ሙሴም ወደዚያ ከገባ በኋላ የደመናው ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆማል፤ እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ያነጋግረው ነበር። ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲያዩ በየድንኳናቸው ደጃፍ ተንበርክከው ይሰግዱ ነበር። ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሔር ሙሴን ፊት ለፊት ያነጋግረው ነበር፤ ከዚያም በኋላ ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ የእርሱ ረዳት የነበረው ወጣት የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “ይህን ሕዝብ ወደዚያች ምድር መርቼ እንድወስድ አዝዘኸኛል፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አልነገርከኝም፤ እኔን እንደምታውቀኝና በእኔም ደስ እንደሚልህ ገልጠህልኛል፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ እንዳገለግልህና አንተን በማስደሰት እንድቀጥል እባክህ መንገድህን አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት።” እግዚአብሔርም “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ሰላምም እሰጥሃለሁ።” አሳርፍህማለሁ አለው። ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከእኛ ጋር የማትወጣ ከሆንክ፥ እኛንም ከዚህ ስፍራ አታውጣን፤ ከእኛ ጋር የማትወጣ ከሆነ በሕዝብህም ሆነ በእኔና በሕዝብህ ደስ መሰኘትህን ሰዎች ሁሉ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? እኛን በምድር ላይ ካሉት ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ የሚያደርገን የአንተ ከእኔና ከሕዝብህ ጋር መሆን አይደለምን?” እግዚአብሔርም ሙሴን “እኔ አንተን በሚገባ በትክክል ስለማውቅህና በአንተም ደስ ስለምሰኝ የምትለውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለው። ሙሴም እግዚአብሔርን “እባክህን ክብርህን አሳየኝ” አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ደግነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ስሜን በፊትህ ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምራለሁ፤ የምራራለትንም እራራለታለሁ፤ ፊቴን አይቶ ለመኖር የሚችል ሰው ስለሌለ ፊቴን ለማየት አትችልም። ነገር ግን እዚህ በአጠገቤ በአለት ላይ የምትቆምበት ስፍራ አለ። የእኔ ክብር በዚያ ሲያልፍ በአለቱ ስንጣቂ አቈይሃለሁ፤ እስካልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ ከዚያም በኋላ እጄን አነሣለሁ፤ አንተም ፊቴን ሳይሆን ጀርባዬን ታያለህ።”
ዘፀአት 33:7-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴ ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈሩ ራቅ አድርጎ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ “የመገናኛ ድንኳን” ብሎ ጠራው። ጌታን የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ በሚሄድበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆምና ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ በሚገባበት ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፤ ጌታም ሙሴን ያናግረው ነበር። ሕዝቡ ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ይሰግድ ነበር። ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ጌታም ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴ ወደ ሰፈሩ ሲመለስ አገልጋዩ የሆነው ወጣቱ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴ ጌታን እንዲህ አለው፥ “እይ! አንተ ‘ይህን ሕዝብ አውጣ’ ብለኸኛል፥ ነገር ግን ከእኔ ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም፦ ‘በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር። አሁንም በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ እንዳውቅህና በፊትህም ሞገስን እንዳገኝ እባክህ መንገድህን አሳየኝ፤ ይህንንም ሕዝብ እንደ ሕዝብህ እየው።” እርሱም “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው። ሙሴም እንዲህ አለው፦ “አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ ከዚህ አታውጣን። እኔና ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? እኔና ሕዝብህ በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ የተለየን የምንሆነው አንተ ከእኛ ጋር በመውጣትህ አይደለምን?” ጌታ ሙሴን፦ “በፊቴ ሞገስን ስላገኘህና በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ” አለው። እርሱም፦ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለ። እርሱም እንዲህ አለው፦ “እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ የጌታንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውን እምራለሁ።” ደግሞም “ሰው አይቶኝ መኖር አይችልምና ፊቴን ማየት አትችልም” አለ። ጌታ እንዲህ አለው፦ “እነሆ የምትቆምበት ስፍራ በአጠገቤ አለ፥ በዓለቱ ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬ ሲያልፍ ዓለቱ ስንጥቅ ውስጥ አስቀምጥሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ በመዳፌ እጋርዳለሁ፤ መዳፌን አነሣለሁ፥ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።”