ዘፀአት 31:1-6
ዘፀአት 31:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ያስተውል ዘንድ በጥበብም፥ በማስተዋልም፥ በዕውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የአናጺዎች አለቃ ይሆን ዘንድ ወርቅንና ብርን፥ ናስንም፥ ብጫና ሰማያዊ፥ እጥፍ ሆኖ የተፈተለ ነጭና ቀይ ሐርን ይሠራ ዘንድ፤ በሥራውም ሁሉ የሚደረገውን የድንጋይ ማለዘብን፥ ከዕንጨትም የሚጠረበውን ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ፥ ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ዕውቅትን ሰጠሁ።
ዘፀአት 31:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ። በሁሉም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራ፣ ብልኀት፣ ችሎታና ዕውቀት እንዲኖረው የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቼዋለሁ። ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣ ድንጋዮችን እንዲቈፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው። በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ፤ እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልኀትን ሰጥቻቸዋለሁ፤
ዘፀአት 31:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ።
ዘፀአት 31:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባጽልኤልን በስም ጠርቼአለሁ። ማንኛውንም የእጅ ጥበብ መሥራት እንዲችል ማስተዋልና ብልኀት የማወቅም ችሎታ ይኖረው ዘንድ በመንፈሴ እንዲሞላ አድርጌአለሁ፤ ስለዚህም በብልኀት የሥራ ዕቅድ እያወጣ ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ ልዩ ልዩ ነገሮችን ይሠራል። እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ ለመቅረጽ፥ እንጨትንም ለመጥረብ፥ ሌላውንም ሥራ ሁሉ በጥበብ ለማከናወን እንዲችል አድርጌዋለሁ። ከእርሱም ጋር እንዲሠራ ከዳን ነገድ የአሒሳማክን ልጅ ኦሆሊአብን መርጬአለሁ፤ እኔ ያዘዝኩህን ነገር ሁሉ እንዲሠሩ ሌሎችም የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ታላቅ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጌአለሁ።
ዘፀአት 31:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በጥበብ፥ በማስተዋል፥ በእውቀትና ሥራ ሁሉ እንዲሠራ የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፥ ልዩ ማስተዋል እንዲኖረው፥ በወርቅ፥ በብርና በነሐስ እንዲሠራ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ እንዲቀርጽ፥ እንጨት እንዲጠርብ፥ ሁሉንም ሥራ እንዲሠራ ሞላሁበት። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሆነውን የአሒሳማክን ልጅ ኤልያብን ሰጥቼዋለሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ እንዲያደርጉ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ላይ ጥበብን አኑሬአለሁ።