ዘፀአት 31:1-18
ዘፀአት 31:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ያስተውል ዘንድ በጥበብም፥ በማስተዋልም፥ በዕውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የአናጺዎች አለቃ ይሆን ዘንድ ወርቅንና ብርን፥ ናስንም፥ ብጫና ሰማያዊ፥ እጥፍ ሆኖ የተፈተለ ነጭና ቀይ ሐርን ይሠራ ዘንድ፤ በሥራውም ሁሉ የሚደረገውን የድንጋይ ማለዘብን፥ ከዕንጨትም የሚጠረበውን ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ፥ ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ዕውቅትን ሰጠሁ። የምስክሩን ድንኳን፥ የቃል ኪዳኑንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፤ የዕጣን መሠዊያውን፥ ገበታውንም፥ ዕቃውንም፥ ከዕቃው ሁሉ የነጻውን መቅረዝ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም፥ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ የሚቀቡትን የቅብዐቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚያጥኑትን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቴን ፈጽሞ ጠብቁ። ለእናንተ በእግዚአብሔር የተቀደሰች ናትና ሰንበቴን ጠብቁ፤ የሚያረክሳትም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፤ ሥራንም በእርስዋ የሠራ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከሕዝብዋ መካከል ተለይታ ትጥፋ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደስች የዕረፍት ሰንበት ናት፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ቃል ኪዳን ዕረፍት ያደርጉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ሥራውን ፈጽሞ ስላረፈ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘለዓለም ምልክት ነው።” እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ ሁለቱን የምስክር ጽላት፥ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላት ለሙሴ ሰጠው።
ዘፀአት 31:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ። በጥበብ፣ በብልኀት፣ ዕውቀትና ማንኛውንም ዐይነት ሙያ እንዲኖረው የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቼዋለሁ። ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በንሓስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣ ድንጋዮችን እንዲቈፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው። በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ። “እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልኀትን ሰጥቻቸዋለሁ፤ “ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋራ፣ ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣ ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ የዕጣኑን መሠዊያ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣ ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣ ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣ እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው። “ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።” ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንድታውቁ ነው። “ ‘ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢያረክሰው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ። ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት። እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤ በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፏልና።’ ” እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ መናገሩን ከፈጸመ በኋላ፣ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላት፣ ሁለቱን የምስክር ጽላት ለርሱ ሰጠው።
ዘፀአት 31:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ። የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፥ ገበታውንም ዕቃውንም፥ ከዕቃው ሁሉ ጋር የነጻውን መቅረዝ፥ የዕጣን መሠዊያውን፥ ለሚቃጠል መሥዋት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፥ በብልሃት የተሠራውንም ልብስ፥ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን የጣፋጭ ሽቱውንም ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ። ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰውም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። ስድስት ቀን ሥራን ሥራ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው። እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።
ዘፀአት 31:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባጽልኤልን በስም ጠርቼአለሁ። ማንኛውንም የእጅ ጥበብ መሥራት እንዲችል ማስተዋልና ብልኀት የማወቅም ችሎታ ይኖረው ዘንድ በመንፈሴ እንዲሞላ አድርጌአለሁ፤ ስለዚህም በብልኀት የሥራ ዕቅድ እያወጣ ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ ልዩ ልዩ ነገሮችን ይሠራል። እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ ለመቅረጽ፥ እንጨትንም ለመጥረብ፥ ሌላውንም ሥራ ሁሉ በጥበብ ለማከናወን እንዲችል አድርጌዋለሁ። ከእርሱም ጋር እንዲሠራ ከዳን ነገድ የአሒሳማክን ልጅ ኦሆሊአብን መርጬአለሁ፤ እኔ ያዘዝኩህን ነገር ሁሉ እንዲሠሩ ሌሎችም የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ታላቅ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጌአለሁ። እንዲሠራ ያዘዝኩትም ይህ ነው፤ የመገናኛው ድንኳን፥ የቃል ኪዳኑ ታቦትና መክደኛው፥ የድንኳኑ መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ ጠረጴዛውና ለእርሱ የሚያስፈልገው ዕቃ፥ የጠራ መቅረዝና ለእርሱ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ፥ የዕጣን መሠዊያው፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያና ለእርሱ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ፥ የመታጠቢያው ሳሕንና ማስቀመጫው፥ አሮንና ልጆቹ በክህነት አገልግሎት ላይ ሲሆኑ የሚጠቀሙባቸው የተዋቡ አልባሳት፥ የቅባቱ ዘይትና ለተቀደሰው ስፍራ የሚሆነው መዓዛው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን፤ ልክ እኔ አንተን ባዘዝኩት ዐይነት እነዚህን ሁሉ ነገሮች ይሠራሉ።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ አዘዘው፤ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ እግዚአብሔር እናንተን ለእኔ የተለየ ሕዝብ አድርጌ የመረጥኳችሁ መሆኔን የሚያሳይ ሆኖ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በእኔና በእናንተ መካከል ጸንቶ የሚኖር ምልክት ስለ ሆነ የዕረፍት ቀን አድርጌ የመረጥኩትን ሰንበትን ጠብቁ፤ የተቀደሰ ስለ ሆነ ሰንበትን የዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ጠብቁት፤ ይህን የሰንበት ቀን የማይጠብቅና የሥራ ቀን አድርጎ የሚጠቀምበት ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። ሥራችሁን ሁሉ የምታከናውኑባቸው ስድስት የሥራ ቀኖች አሉላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእኔ ተለይቶ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራበት ሁሉ በሞት ይቀጣ። የእስራኤል ሕዝብ ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ ይህ ቀን ጸንቶ የሚኖር የቃል ኪዳን ምልክት አድርገው ይጠብቁት፤ እኔ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ ከፈጠርኩ በኋላ ሰባተኛው ቀን ሥራዬን አቁሜ ያረፍኩበት ስለ ሆነ በእኔና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር ምልክት ይሁን።” እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ማነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ በእግዚአብሔር ጣት በድንጋይ ላይ የተጻፈባቸውን ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላቶች ሰጠው።
ዘፀአት 31:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እይ! ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በጥበብ፥ በማስተዋል፥ በእውቀትና ሥራ ሁሉ እንዲሠራ የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፥ ልዩ ማስተዋል እንዲኖረው፥ በወርቅ፥ በብርና በነሐስ እንዲሠራ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ እንዲቀርጽ፥ እንጨት እንዲጠርብ፥ ሁሉንም ሥራ እንዲሠራ ሞላሁበት። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሆነውን የአሒሳማክን ልጅ ኤልያብን ሰጥቼዋለሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ እንዲያደርጉ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ላይ ጥበብን አኑሬአለሁ። የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩን ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑን ዕቃ በሙሉ፥ ገበታውና ዕቃው ሁሉ፥ ንጹሑን መቅረዝና ዕቃውን፥ የዕጣን መሠዊያውን፥ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያ ሳሕንና መቀመጫውን፥ በብልሃት የተሠራውን ልብስ፥ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑ የአሮን የተቀደሱ ልብሶች የልጆቹ ልብሶች፥ የቅባቱን ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ እንዲሁ ያድርጉ።” ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ ግን ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ፥ ይህ የምቀድሳችሁ ጌታ እኔ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ለትውልዶቻችሁ ምልክት ነውና። ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰው ፈጽሞ ይገደል፥ በእርሷ ሥራን የሚሠራ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። የእስራኤል ልጆች ሰንበትን ይጠብቁ፤ ሰንበትን መጠበቅ ለትውልዳቸው የዘለዓለም ቃል ኪዳን ያድርጉት። በእኔና በእስራኤል ልጆች መካከል የዘለዓለም ምልክት ነው፤ ጌታ ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ፈጥሮአልና፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው አርፎአልና፥ ተነቃቅቶአልና።’” በሲና ተራራ ከሙሴ ጋር ንግግሩን ከፈጸመ በኋላ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች የሆኑ ሁለት የምስክር ጽላቶችን ሰጠው።