ዘፀአት 3:15-22
ዘፀአት 3:15-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳግመኛም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፥ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘለዓለም ስሜ ነው፤ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ፤ እንዲህም በላቸው፦ የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተገለጠልኝ፦ መጐብኘትን ጐበኘኋችሁ፤ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ ከግብፅ መከራ ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኬጤዎናውያን፥ ወደ አሞሬዎናውያን፥ ወደ ፌርዜዎናውያን፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያን፥ ወደ ኤዌዎናውያን፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያን ሀገር፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ሀገር አወጣችኋለሁ፤ እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትገባላችሁ፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ጠርቶናል፤ አሁንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን ትሉታላችሁ። ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። እኔም እጄን እዘረጋለሁ፤ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቋችኋል። በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ በምትሄዱም ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤ ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤቷ፥ በቤቷም ካለችው ሴት የብር ዕቃ፥ የወርቅ ዕቃ፥ ልብስም ትዋሳለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይም ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።”
ዘፀአት 3:15-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው። “ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብፅ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ። ስለዚህም በግብፅ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ። “የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ። የግብፅ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በስተቀር መቼም እንደማይለቅቃችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብፃውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቃችኋል። “ይህ ሕዝብ በግብፃውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም። እያንዳንዷ ዕብራዊት ከጎረቤቷም ይሁን አብራት ከምትኖረው ግብፃዊት የብርና የወርቅ ጌጣጌጦች እንደዚሁም ልብስ እንድትሰጣት ትጠይቅ። እነዚህንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታስጌጧቸዋላችሁ፤ ታለብሷቸዋላችሁም። በዚህም መንገድ የግብፃውያኑን ሀብት በእጃችሁ አግብታችሁ ትወጣላችሁ።”
ዘፀአት 3:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደናንተ ላከኝ፤’ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ፦ ‘እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ፦ መጎብኘትን ጎበኘኋችሁ፤ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ፤ አልሁ ብሎ ተገለጠልኝ፤’ በላቸው። እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትገባላችሁ፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ አሁንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ’ ትሉታላችሁ። ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። እኔም እጄን እዘረጋለሁ፤ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በሄዳችሁ ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤ ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር ዕቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።”
ዘፀአት 3:15-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም እንደገና ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ይህ የዘለዓለም ስሜ ነው፤ በዚህም ስም ከትውልድ እስከ ትውልድ እታወቃለሁ። እንግዲህ ሂድና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እኔ እግዚአብሔር የተገለጥኩልህ መሆኔንም ንገራቸው፤ ወደ እነርሱ ወርጄ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ ያደረሱባቸውን ግፍና ጭቈና መመልከቴን ንገራቸው። በግፍ ጭቈና ከሚሠቃዩባት ከግብጽ ምድር አውጥቼ እነሆ ዛሬ፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገች ሰፊና ለም የሆነች ምድር ልሰጣቸው ቃል ገብቻለሁ። “ሕዝቤም አንተ የምትነግራቸውን ሁሉ ይሰማሉ፤ ከዚያም በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ አለቆች ጋር ሆነህ ወደ ግብጽ ንጉሥ ሂድና ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገልጦልናል፤ ስለዚህም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ተጒዘን ወደ በረሓ እንድንሄድ ፍቀድልን’ ብላችሁ ንገሩት። እርግጥ ነው በታላቅ ክንድ ካልተገደደ በቀር የግብጽ ንጉሥ እንደማይለቃችሁ ዐውቃለሁ። ስለዚህም እጅግ አስፈሪ የሆኑ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የኀይል ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እቀጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትወጡ ይፈቅድላችኋል። “በምትወጡበት ጊዜ ሕዝቡ በግብጻውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ ስለማደርግ ባዶ እጃችሁን አትወጡም። የዕብራውያን ሴቶች እያንዳንዳቸው ጐረቤት በመሆን አብረዋቸው የሚኖሩትን ግብጻውያን ሴቶች ወርቅ፥ ብርና፥ ጌጣጌጥና ልብስ እንዲሰጡአቸው ይጠይቃሉ፤ ይህንንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታለብሳላችሁ፤ በዚህም ዐይነት ግብጻውያንን በዝብዛችሁ ትወጣላችሁ።”
ዘፀአት 3:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘ጌታ የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ፤’ ይህ ለዘለዓለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።” ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ትሰበስባለህ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ “ጌታ የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ፥ የያዕቆብም ተገለጠልኝ፤ እንዲህም አለኝ ‘ጎበኘኋችሁ፥ በግብጽም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብጽም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ።’ እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብጽ ንጉሥ ትሄዳላችሁ፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ጌታ ተገለጠልን፤ ስለዚህ ለአምላካችን ለጌታ እንድንሠዋ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ’ ትሉታላችሁ። ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር የግብጽ ንጉሥ እንድትሄዱ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብጽን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ እንዲህም ይሆናል፥ በሄዳችሁ ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤ ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር እቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።”