ዘፀአት 19:1-8
ዘፀአት 19:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሦስተኛው ወር በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ጠርቶ አለው፥ “ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ንገር፤ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ እንደ ንስር ክንፍም እንደ ተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ፥ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ። እናንተም የክህነት መንግሥት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ ይህንም ቃል ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።” ሙሴም መጣ፤ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። ሕዝቡም ሁሉ አንድ ቃል ሆነው፥ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እንሰማለን፤ እናደርጋለንም” ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ።
ዘፀአት 19:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሦስተኛው ወር እስራኤላውያን ከግብፅ ለቀው በወጡበት በዚያችው ዕለት ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። ከራፊዲም ከተነሡ በኋላ ወደ ሲና ምድረ በዳ ገቡ፤ እስራኤልም በዚያ በምድረ በዳው በተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ። ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወጣ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከተራራው ጠራውና እንዲህ አለው፤ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው ለእስራኤልም ሕዝብ የምትናገረው ይህ ነው፤ ‘በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው።” ስለዚህ ሙሴ ተመልሶ የሕዝቡን አለቆች አስጠራ፤ እንዲናገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ቃሎች ሁሉ ነገራቸው። ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ስለዚህ ሙሴ እነርሱ ያሉትን መልሶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወሰደ።
ዘፀአት 19:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው፦ ለያቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር፦ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደ ተሸከም ኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግስት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው። ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው፦ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ።
ዘፀአት 19:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያው በመጀመሪያው ቀን ወደ ሲና በረሓ ደረሱ፤ እነርሱም ከረፊዲም ተነሥተው ወደ ሲና በረሓ ተጒዘው በተራራው ፊት ለፊት ባለው በረሓ ሰፈሩ። ሙሴም ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደ ተራራው ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ላይ በመናገር የያዕቆብ ተወላጆች ለሆኑት እስራኤላውያን እንዲህ ብሎ እንዲናገር አዘዘው፥ “ ‘እኔ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረግኹትንና ንስር ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ እንደምትሸከም እኔም እናንተን እስከዚህ ስፍራ እንዴት ወደ እኔ እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል፤ አሁንም እነሆ፥ ለእኔ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔንም ብትጠብቁ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆን የተለያችሁ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ ለእኔም ብቻ የተለያችሁ ቅዱሳን ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ እንደ ካህናትም ሆናችሁ ታገለግሉኛላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይኸው ነው።” ስለዚህም ሙሴ ከተራራ ወርዶ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ በአንድነት በመጥራት እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ ሁሉም በአንድ ድምፅ ተባብረው “እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ እንፈጽማለን” አሉ፤ ሙሴም ይህንኑ ለእግዚአብሔር አቀረበ።
ዘፀአት 19:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ወጣ፤ ጌታም ከተራራው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር፦ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንዴት እንደ ተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ የካህናት መንግስት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።” ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ ጌታ ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት ሆነው፦ “ጌታ ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ ጌታ አደረሰ።