ኦሪት ዘጸአት 19
19
እስራኤላውያን በሲና ተራራ
1እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያው በመጀመሪያው ቀን ወደ ሲና በረሓ ደረሱ፤ 2እነርሱም ከረፊዲም ተነሥተው ወደ ሲና በረሓ ተጒዘው በተራራው ፊት ለፊት ባለው በረሓ ሰፈሩ። 3ሙሴም ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደ ተራራው ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ላይ በመናገር የያዕቆብ ተወላጆች ለሆኑት እስራኤላውያን እንዲህ ብሎ እንዲናገር አዘዘው፥ 4“ ‘እኔ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረግኹትንና ንስር ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ እንደምትሸከም እኔም እናንተን እስከዚህ ስፍራ እንዴት ወደ እኔ እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል፤ 5አሁንም እነሆ፥ ለእኔ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔንም ብትጠብቁ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆን የተለያችሁ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ #ዘዳ. 4፥20፤ 7፥6፤ 14፥2፤ 26፥18፤ ቲቶ 2፥14። #1ጴጥ. 2፥9። 6ለእኔም ብቻ የተለያችሁ ቅዱሳን ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ እንደ ካህናትም ሆናችሁ ታገለግሉኛላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይኸው ነው።” #ራዕ. 1፥6፤ 5፥10። 7ስለዚህም ሙሴ ከተራራ ወርዶ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ በአንድነት በመጥራት እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ ነገራቸው። 8ከዚህም በኋላ ሁሉም በአንድ ድምፅ ተባብረው “እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ እንፈጽማለን” አሉ፤ ሙሴም ይህንኑ ለእግዚአብሔር አቀረበ።
9እግዚአብሔርም ሙሴን “እኔ ግዙፍ በሆነ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ስለዚህም ሕዝቡ እኔ ከአንተ ጋር ስነጋገር በመስማት ከአሁን ጀምሮ አንተ የምትለውን ሁሉ ያምናሉ።”
ሙሴም ሕዝቡ የሰጠውን መልስ ወደ እግዚአብሔር አቀረበ፤ 10እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፥ “ወደ ሰዎቹ ሂድ፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ አድርገህ ታቀርባቸው ዘንድ ዛሬና ነገ ሰውነታቸውን እንዲያነጹና ልብሳቸውንም እንዲያጥቡ ንገራቸው፤ 11በሦስተኛው ቀን በሕዝቡ ፊት በሲና ተራራ ላይ እኔ እግዚአብሔር ስለምወርድ ሁሉም በዚያ ቀን ይዘጋጁ። 12በተራራው ዙሪያ ድንበር አብጅ፤ እነርሱም ያንን ድንበር አልፈው ወደ ተራራው እንዳይወጡና እንዲያውም ድንበሩን እንዳይነኩ ንገራቸው፤ ማንም ሰው ከተወሰነው ድንበር አልፎ፥ ተራራውን ቢነካ በሞት ይቀጣ፤ 13ይኸውም ማንም ሳይነካው በድንጋይ ተወግሮ ወይም በፍላጻ ተወግቶ ይገደል፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎችም ሆኑ እንስሶች በዚሁ ዐይነት ይገደሉ፤ ሕዝቡ ወደ ተራራው መውጣት የሚገባው ለረጅም ጊዜ መለከት ሲነፋ ብቻ ነው።” #ዕብ. 12፥18-20።
14ከዚህ በኋላ ሙሴ ከተራራው ወርዶ ሕዝቡ ልብሱን አጥቦ እንዲቀደስ አደረገ፤ 15ሙሴም ሰዎቹን “ለተነገወዲያው ዕለት ተዘጋጁ፤ እስከዚያም ቀን ድረስ ወደ ሴት አትቅረቡ” አላቸው።
16በሦስተኛው ቀን ማለዳ የነጐድጓድ ድምፅ አስተጋባ፤ የመብረቅ ብልጭልጭታና ጥቅጥቅ ያለ ደመና በተራራው ላይ ታየ፤ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የእምቢልታ ድምፅ ተሰማ። ሰዎቹም በሰፈሩበት ቦታ ፈርተው ተንቀጠቀጡ። #ራዕ. 4፥5። 17ሙሴም ከሰፈር እየመራ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ እነርሱም በተራራው እግር ሥር ቆሙ። 18እግዚአብሔር በእሳት ስለ ወረደበት መላው የሲና ተራራ በጢስ ተሞላ። ጢሱም ከእሳት ምድጃ እንደሚወጣ ዐይነት ሆኖ ወደ አየር ተትጐለጐለ፤ ሰዎቹም እጅግ ፈርተው ተንቀጠቀጡ። #ዘዳ. 4፥11-12። 19የእምቢልታውም ብርቱ ድምፅ እያከታተለ ማስተጋባት ቀጠለ፤ ሙሴ ሲናገር እግዚአብሔር በነጐድጓድ ይመልስለት ነበር፤ 20እግዚአብሔር በሲና ተራራ ራስ ላይ ወርዶ፥ ወደ ተራራው ጫፍ እንዲመጣ ሙሴን ጠራው፤ ሙሴም ወደ ተራራው ጫፍ ወጣ፤ 21እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔን እግዚአብሔርን ለማየት የተወሰነውን ክልል አልፈው እንዳይመጡ ወርደህ ለሕዝቡ ንገር፤ ይህን ቢያደርጉ ግን ከእነርሱ ብዙዎቹ ይሞታሉ፤ 22ለአገልግሎት ወደ እኔ የሚቀርቡ ካህናት እንኳ ሳይቀሩ ራሳቸውን ያንጹ፤ ይህ ካልሆነ እኔ እግዚአብሔር እቀጣቸዋለሁ።”
23ሙሴም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር መለሰ፦ “ቦታው ቅዱስ ስለ ሆነ ከዚህ ራቁ ብለህ ስለ አስጠነቀቅከን ሕዝቡ ወደ ተራራው ሊወጣ አይችልም።”
24እግዚአብሔርም “ውረድና አሮንን ይዘህ ና፤ ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ ወደ እኔ ለመውጣት ወሰኑን ማለፍ የለባቸውም፤ ይህን ቢያደርጉ ግን እኔ እግዚአብሔር እቀጣቸዋለሁ።” 25ሙሴም ወደ እነርሱ ወርዶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 19: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997