የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 14:10-31

ዘፀአት 14:10-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ፈር​ዖ​ንም በቀ​ረበ ጊዜ የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ዐይ​ና​ቸ​ውን አነሡ፤ እነ​ሆም፥ ግብ​ፃ​ው​ያን ሲከ​ተ​ሉ​አ​ቸው አዩ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጮኹ። ሙሴ​ንም አሉት፥ “በግ​ብፅ መቃ​ብር ስላ​ል​ኖረ በም​ድረ በዳ እን​ሞት ዘንድ አወ​ጣ​ኸን? ከግ​ብፅ ታወ​ጣን ዘንድ ይህ ያደ​ረ​ግ​ህ​ብን ምን​ድን ነው? በም​ድረ በዳ ከም​ን​ሞት ብን​ገ​ዛ​ላ​ቸው ይሻ​ለ​ና​ልና፦ ‘ተወን፤ ለግ​ብ​ፃ​ው​ያን እን​ገዛ’ ብለን በግ​ብፅ ሳለን ያል​ንህ ቃል ይህ አይ​ደ​ለ​ምን?” ሙሴም ለሕ​ዝቡ፥ “አት​ፍሩ፤ ዛሬ የም​ታ​ዩ​አ​ቸ​ውን ግብ​ፃ​ው​ያ​ንን ለዘ​ለ​ዓ​ለም አታ​ዩ​አ​ቸ​ው​ምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእ​ና​ንተ የሚ​ያ​ደ​ር​ጋ​ትን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ማዳን እዩ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ እና​ንተ ይዋ​ጋል፤ እና​ን​ተም ዝም ትላ​ላ​ችሁ” አላ​ቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮ​ኽ​ብ​ኛ​ለህ? ከብ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን እን​ዲ​ነዱ ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ንገር። አን​ተም በት​ር​ህን አንሣ፤ እጅ​ህ​ንም በባ​ሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈ​ለ​ውም፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች በባ​ሕሩ ውስጥ በየ​ብስ ያል​ፋሉ። እነ​ሆም፥ እኔ የፈ​ር​ዖ​ን​ንና የግ​ብ​ፃ​ው​ያ​ንን ልብ አጸ​ና​ለሁ፤ በኋ​ላ​ቸ​ውም ይገ​ባሉ፤ በፈ​ር​ዖ​ንና በሠ​ራ​ዊ​ቱም ሁሉ፥ በሰ​ረ​ገ​ሎ​ቹም፥ በፈ​ረ​ሰ​ኞ​ቹም ላይ እከ​ብ​ራ​ለሁ። ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም በፈ​ር​ዖ​ንና በሰ​ረ​ገ​ሎቹ፥ በፈ​ረ​ሰ​ኞ​ቹም ላይ ክብር በአ​ገ​ኘሁ ጊዜ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ሆንሁ ያው​ቃሉ።” በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሠራ​ዊት ፊት ይሄድ የነ​በ​ረው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አክ ፈቀቅ ብሎ በኋ​ላ​ቸው ሄደ፤ የደ​መ​ና​ውም ዐምድ ከፊ​ታ​ቸው ፈቀቅ ብሎ በኋ​ላ​ቸው ቆመ፤ በግ​ብ​ፃ​ው​ያን ሰፈ​ርና በእ​ስ​ራ​ኤል ሰፈር መካ​ከ​ልም ገባ፤ በዚ​ያም ጭጋ​ግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊ​ቱም አለፈ፤ ሌሊ​ቱ​ንም ሁሉ እርስ በእ​ር​ሳ​ቸው አል​ተ​ቃ​ረ​ቡም። ሙሴም በባ​ሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሌሊ​ቱን ሁሉ ጽኑ የአ​ዜብ ነፋስ አም​ጥቶ ባሕ​ሩን አስ​ወ​ገ​ደው፤ ባሕ​ሩ​ንም አደ​ረ​ቀው፤ ውኃ​ውም ተከ​ፈለ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች በባ​ሕሩ መካ​ከል በየ​ብስ ገቡ፤ ውኃ​ውም በቀ​ኛ​ቸ​ውና በግ​ራ​ቸው እንደ ግድ​ግዳ ሆነ​ላ​ቸው። ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም፥ የፈ​ር​ዖን ፈረ​ሶ​ችና ሰረ​ገ​ሎች፥ ፈረ​ሰ​ኞ​ቹም ሁሉ እያ​ሳ​ደዱ በኋ​ላ​ቸው ወደ ባሕር መካ​ከል ገቡ። ንጋ​ትም በሆነ ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በእ​ሳ​ትና በደ​መና ዐምድ ሆኖ የግ​ብ​ፃ​ው​ያ​ንን ሠራ​ዊት ተመ​ለ​ከተ፤ የግ​ብ​ፃ​ው​ያ​ን​ንም ሠራ​ዊት አወከ። የሰ​ረ​ገ​ሎ​ቹ​ንም መን​ኰ​ራ​ኵር አሰረ፤ ወደ ጭን​ቅም አገ​ባ​ቸው፤ ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ እነ​ርሱ ይዋ​ጋ​ላ​ቸ​ዋ​ልና ከእ​ስ​ራ​ኤል ፊት እን​ሽሽ” አሉ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን አለው፥ “እጅ​ህን በባ​ሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃ​ውም በግ​ብ​ፃ​ው​ያን፥ በሰ​ረ​ገ​ሎ​ቻ​ቸ​ውም፥ በፈ​ረ​ሰ​ኞ​ቻ​ቸ​ውም ላይ ይመ​ለስ፤ ይሸ​ፍ​ና​ቸ​ውም።” ሙሴም እጁን በባ​ሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕ​ሩም ማለዳ ወደ መፍ​ሰሱ ተመ​ለሰ፤ ግብ​ፃ​ው​ያ​ንም ከእ​ርሱ ሸሹ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ግብ​ፃ​ው​ያ​ንን በባ​ሕሩ መካ​ከል ጣላ​ቸው። ውኃ​ውም ተመ​ልሶ በኋ​ላ​ቸው ወደ ባሕር የገ​ቡ​ትን ሰረ​ገ​ሎ​ችን፥ ፈረ​ሰ​ኞ​ች​ንም፥ የፈ​ር​ዖ​ን​ንም ሠራ​ዊት ሁሉ ከደነ፤ ከመ​ጡ​ትም ሁሉ አንድ ስንኳ የቀረ የለም። የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ግን በባ​ሕሩ ውስጥ በየ​ብስ ሄዱ፤ ውኃ​ውም በቀ​ኛ​ቸ​ውና በግ​ራ​ቸው እንደ ግድ​ግዳ ሆነ​ላ​ቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በዚያ ቀን እስ​ራ​ኤ​ልን ከግ​ብ​ፃ​ው​ያን እጅ አዳ​ና​ቸው፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ግብ​ፃ​ው​ያን እንደ ሞቱ በባ​ሕር ዳር አዩ። እስ​ራ​ኤ​ልም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በግ​ብ​ፃ​ው​ያን ላይ ያደ​ረ​ጋ​ትን ታላ​ቂ​ቱን እጅ አዩ፤ ሕዝ​ቡም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፈሩ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አመኑ፤ ባሪ​ያ​ው​ንም ሙሴን አከ​በሩ።

ዘፀአት 14:10-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኹ። እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብፅ አውጥተህ ምን አደረግህልን? በግብፅ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብፃውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!” ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብፅና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ። ግብፃውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሰረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ። ሲነጋጋም እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብፃውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው። መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤ ግብፃውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር (ያህዌ) ግብፅን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ውሃው ግብፃውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብፃውያን ከውሃው ሸሹ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ግብፃውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የግብፅ ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም። እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ። በዚያች ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብፃውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ። እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በባሪያው በሙሴም አመኑ።

ዘፀአት 14:10-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግሠው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። ሙሴንም “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ‘በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፦ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ፤” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፤ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኮራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ፤” አሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውኃውም በግብፃውያን፥ በሰረገሎቻቸውም፥ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ፤” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን፥ ፈረሰኞችንም፥ የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልተረፈም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው። እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።

ዘፀአት 14:10-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እስራኤላውያን ንጉሡና ሠራዊቱ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል መምጣታቸውን አይተው እጅግ ፈሩ፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “ከቶ በግብጽ የመቃብር ቦታ አልነበረምን? ታዲያ በዚህ በረሓ እንድንሞት ያመጣኸን ለምንድን ነው? ከግብጽ አውጥተኸን ምን እንደ ደረሰብን እስቲ ተመልከት! ይህ ሁሉ እንደሚሆን ገና ከዚያ ሳንወጣ ነግረንህ አልነበረምን? እንዲያውም ‘እባክህ ተወን፥ ለግብጻውያን ባርያዎች ሆነን እናገልግል’ ብለንህ ነበር፤ በእርግጥም በዚህ በረሓ ከመሞት፥ በዚያ ባርያዎች ሆነን መኖር በተሻለን ነበር።” ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ! ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር እናንተን ለማዳን የሚያደርገውን ዛሬ ታያላችሁ፤ እነዚህን ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ማድረግ የሚገባችሁ ጸጥ ብላችሁ ሁኔታውን መጠበቅ ብቻ ነው።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ የምትጮኸው ለምንድን ነው? ይልቅስ ሰዎቹን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ በትርህን አንሣ፤ በባሕሩም ላይ ዘርጋው፤ ውሃውም ከሁለት ይከፈላል፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን አቋርጠው ይሄዳሉ፤ የግብጻውያንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን ያሳድዳሉ፤ ንጉሡንና ሠራዊቱን፥ ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በመንሣት ክብርን እጐናጸፋለሁ። እነርሱንም በማሸንፍበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” የእስራኤልን ሠራዊት ፊት ፊት ይመራ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ኋላ ተመልሶ ደጀን ሆነ፤ የደመናውም ዐምድ አልፎ በኋላ በኩል ቆመ፤ ደመናውም በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል መጥቶ ግብጻውያንን በጨለማ ሲጋርድ ለእስራኤል ሕዝብ ግን ብርሃን ይሰጥ ነበር፤ ስለዚህ የግብጽ ሠራዊት ሌሊቱን ሙሉ ወደ እስራኤላውያን መጠጋት አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ የምሥራቅ ነፋስ ባሕሩን ወደ ኋላ መለሰው፤ ነፋሱም ሌሊቱን ሙሉ በመንፈሱ፥ ባሕሩን ወደ ደረቅ ምድር ለወጠው፤ ውሃውም ከሁለት ተከፈለ፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻግረው ሄዱ፤ ውሃውም በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ ነበር። ግብጻውያንም በሠረገሎቻቸው፥ በፈረሶቻቸውና በፈረሰኞቻቸው እየተረዱ አሳደዱአቸው፤ ተከታትለዋቸውም ወደ ባሕሩ ገቡ። ገና ጎሕ ሳይቀድ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሠራዊት በተመለከተ ጊዜ ሁሉም በፍርሃት ተጨነቁ። እግዚአብሔር የሠረገላዎቻቸውን መንኰራኲሮች ከመሬት ጋር ስላጣበቀባቸው ሠረገሎቻቸውን ነድተው ማንቀሳቀስ አልቻሉም፤ ግብጻውያንም፥ “እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ረድቶ እኛን እየተዋጋን ነው፤ ስለዚህ ከፊታቸው እንሽሽ!” ተባባሉ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ውሃውም በግብጻውያን፥ በሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ይመለስባቸው” አለው። ስለዚህ ሙሴ እጁን ወደ ባሕሩ ዘረጋ፤ ጎሕ ሲቀድ ውሃው ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ፤ ግብጻውያንም ከውሃው ሸሽተው ለመውጣት ሞከሩ፤ እግዚአብሔር ግን በባሕር ውስጥ ጣላቸው። ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ይከተሉ የነበሩትን ሠረገሎችን፥ ፈረሰኞችንና መላውን የግብጽ ሠራዊት ሸፈነ፤ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም። እስራኤላውያን ግን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ ስለ ቆመላቸው በደረቅ ምድር ተሻገሩ። በዚያን ቀን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ በባሕር ሸሸ የተረፈረፈውንም የግብጻውያንን ሬሳ ተመለከቱ። እግዚአብሔር በእንዴት ያለ ታላቅ ኀይል ግብጻውያንን እንዳሸነፈ እስራኤላውያን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።

ዘፀአት 14:10-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን ከኋላቸው እየመጡ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ ጌታም ጮኹ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “በግብጽ መቃብር ስለ ሌለ ነው በምድረ በዳ እንድንሞት ያወጣኸን? ከግብጽ አውጥተህ ምንድነው ያደረግህብን? በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? ተወን፥ ግብፃውያንን እናገልግል፤ በምድረ በዳ ከምንሞት ብናገለግላቸው ይሻላልና።” ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የጌታን ማዳን እዩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና። ጌታ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ ጌታ በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠፈር ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠፈር አወከ። የሰረገሎቹንም ጎማ አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አስገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “ጌታ ግብፃውያንን ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኆቹም በግብፃውያን ላይ በሰረገሎቻቸው ላይ በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ” አለው። ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ ጌታም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። ውኆቹም ተመልሰው በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችን የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደኑ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተራመዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆኑላችው። ጌታም በዚያን ቀን እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሞት በባሕር ዳር አዩ። እስራኤልም ጌታ በግብጽ ላይ ያደረጋትን ታላቅ ኃይል አየ፥ ሕዝቡም ጌታን ፈሩ፥ በጌታና በአገልጋዩ በሙሴ አመኑ።