ዘፀአት 14:10-18
ዘፀአት 14:10-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም፥ ግብፃውያን ሲከተሉአቸው አዩ፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ሙሴንም አሉት፥ “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናልና፦ ‘ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” ሙሴም ለሕዝቡ፥ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም፥ እኔ የፈርዖንንና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ፥ በሰረገሎቹም፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር በአገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
ዘፀአት 14:10-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኹ። እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብፅ አውጥተህ ምን አደረግህልን? በግብፅ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብፃውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!” ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
ዘፀአት 14:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግሠው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። ሙሴንም “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ‘በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፦ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ፤” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
ዘፀአት 14:10-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤላውያን ንጉሡና ሠራዊቱ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል መምጣታቸውን አይተው እጅግ ፈሩ፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “ከቶ በግብጽ የመቃብር ቦታ አልነበረምን? ታዲያ በዚህ በረሓ እንድንሞት ያመጣኸን ለምንድን ነው? ከግብጽ አውጥተኸን ምን እንደ ደረሰብን እስቲ ተመልከት! ይህ ሁሉ እንደሚሆን ገና ከዚያ ሳንወጣ ነግረንህ አልነበረምን? እንዲያውም ‘እባክህ ተወን፥ ለግብጻውያን ባርያዎች ሆነን እናገልግል’ ብለንህ ነበር፤ በእርግጥም በዚህ በረሓ ከመሞት፥ በዚያ ባርያዎች ሆነን መኖር በተሻለን ነበር።” ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ! ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር እናንተን ለማዳን የሚያደርገውን ዛሬ ታያላችሁ፤ እነዚህን ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ማድረግ የሚገባችሁ ጸጥ ብላችሁ ሁኔታውን መጠበቅ ብቻ ነው።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ የምትጮኸው ለምንድን ነው? ይልቅስ ሰዎቹን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ በትርህን አንሣ፤ በባሕሩም ላይ ዘርጋው፤ ውሃውም ከሁለት ይከፈላል፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን አቋርጠው ይሄዳሉ፤ የግብጻውያንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን ያሳድዳሉ፤ ንጉሡንና ሠራዊቱን፥ ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በመንሣት ክብርን እጐናጸፋለሁ። እነርሱንም በማሸንፍበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”
ዘፀአት 14:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን ከኋላቸው እየመጡ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ ጌታም ጮኹ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “በግብጽ መቃብር ስለ ሌለ ነው በምድረ በዳ እንድንሞት ያወጣኸን? ከግብጽ አውጥተህ ምንድነው ያደረግህብን? በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? ተወን፥ ግብፃውያንን እናገልግል፤ በምድረ በዳ ከምንሞት ብናገለግላቸው ይሻላልና።” ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የጌታን ማዳን እዩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና። ጌታ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።”