ዘፀአት 14:1-21
ዘፀአት 14:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ተመልሰው በመግደሎና በባሕር መካከል፥ በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻር እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ። ፈርዖንም ለሕዝቡ ስለ እስራኤል ልጆች፦ ‘በምድር ይቅበዘበዛሉ፤ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው’ ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ እርሱም ከኋላቸው ይከተላቸዋል፤ እኔም በፈርዖንና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ እከብራለሁ፤ ግብፃውያንም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የሹሞቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፥ “እንዳይገዙልን የእስራኤልን ልጆች የለቀቅነው ምን ማድረጋችን ነው?” አሉ። ፈርዖንም ሰረገላውን አሰናዳ፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ሰበሰበ። ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ ወስዶ ሁሉንም ከሦስት ከፈላቸው። እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንንና የሹሞቹን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሰረገሎቹም፥ ፈረሰኞቹም፥ ሠራዊቱም ሁሉ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻርም ሰፍረው አገኙአቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም፥ ግብፃውያን ሲከተሉአቸው አዩ፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ሙሴንም አሉት፥ “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናልና፦ ‘ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” ሙሴም ለሕዝቡ፥ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም፥ እኔ የፈርዖንንና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ፥ በሰረገሎቹም፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር በአገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የአዜብ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ።
ዘፀአት 14:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። ‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ። የግብፅ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብፅ ሠረገላዎች ጋር ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። እግዚአብሔር (ያህዌ) የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብፅ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። ግብፃውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣ ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበአልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው። ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኹ። እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብፅ አውጥተህ ምን አደረግህልን? በግብፅ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብፃውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!” ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብፅና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ።
ዘፀአት 14:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባህር ዳር ትሰፍራላችሁ። ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ ‘በምድር ይቅበዘበዛሉ፤ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው፤’ ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም እንደ ኮበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል?” አሉ። ሰረገላውንም አሰናዳ፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ። እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዐይናቸውን አነሡ፤ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግሠው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። ሙሴንም “በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ‘በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና ተወን፤ ለግብፃውያን እንገዛ’ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፦ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ፤” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፤ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ።
ዘፀአት 14:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን ተመልሰው፥ በሚግዶልና በቀይ ባሕር መካከል ባለው ፒሃሒሮት ፊት ለፊት በባዓልጸፎን አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው። እነሆ፥ ንጉሡ እስራኤላውያን በበረሓ ተዘግተው በአገሪቱ ዙሪያ የሚንከራተቱ ይመስለዋል። እኔም ልቡን ስለማደነድነው ያሳድዳችኋል፤ ስለዚህም በንጉሡና በሠራዊቱ ላይ የምጐናጸፈው ድል ለእኔ ክብር ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ። የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ ማምለጣቸው በተነገረው ጊዜ እርሱና መኳንንቱ ሐሳባቸውን ለውጠው “ይህ ያደረግነው ነገር ምንድን ነው? እስራኤላውያን አምልጠው እንዲሄዱ ስንፈቅድ አገልጋዮቻችንን ሁሉ ማጣታችን አይደለምን?” አሉ። ንጉሡም ሠረገላውን አዘጋጅቶ ሠራዊቱን አንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገሎችን ጨምሮ በግብጽ ያሉትን ሠረገሎች ሁሉ አሰለፈ፤ የጦር አዛዦችንም መደበላቸው፤ እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ በድፍረት በመውጣት ላይ የነበሩትን እስራኤላውያንን አሳደዳቸው፤ የግብጽ ሠራዊት በፈረሶችና በሠረገላዎች ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ ተከታተላቸው፤ በቀይ ባሕር ፊት ለፊት ባሉት በፒሃሒሮት በባዓልጸፎን አጠገብ በሰፈሩበት ቦታ ደረሱባቸው። እስራኤላውያን ንጉሡና ሠራዊቱ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል መምጣታቸውን አይተው እጅግ ፈሩ፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “ከቶ በግብጽ የመቃብር ቦታ አልነበረምን? ታዲያ በዚህ በረሓ እንድንሞት ያመጣኸን ለምንድን ነው? ከግብጽ አውጥተኸን ምን እንደ ደረሰብን እስቲ ተመልከት! ይህ ሁሉ እንደሚሆን ገና ከዚያ ሳንወጣ ነግረንህ አልነበረምን? እንዲያውም ‘እባክህ ተወን፥ ለግብጻውያን ባርያዎች ሆነን እናገልግል’ ብለንህ ነበር፤ በእርግጥም በዚህ በረሓ ከመሞት፥ በዚያ ባርያዎች ሆነን መኖር በተሻለን ነበር።” ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ! ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር እናንተን ለማዳን የሚያደርገውን ዛሬ ታያላችሁ፤ እነዚህን ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ማድረግ የሚገባችሁ ጸጥ ብላችሁ ሁኔታውን መጠበቅ ብቻ ነው።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ የምትጮኸው ለምንድን ነው? ይልቅስ ሰዎቹን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ በትርህን አንሣ፤ በባሕሩም ላይ ዘርጋው፤ ውሃውም ከሁለት ይከፈላል፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን አቋርጠው ይሄዳሉ፤ የግብጻውያንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን ያሳድዳሉ፤ ንጉሡንና ሠራዊቱን፥ ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በመንሣት ክብርን እጐናጸፋለሁ። እነርሱንም በማሸንፍበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” የእስራኤልን ሠራዊት ፊት ፊት ይመራ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ኋላ ተመልሶ ደጀን ሆነ፤ የደመናውም ዐምድ አልፎ በኋላ በኩል ቆመ፤ ደመናውም በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል መጥቶ ግብጻውያንን በጨለማ ሲጋርድ ለእስራኤል ሕዝብ ግን ብርሃን ይሰጥ ነበር፤ ስለዚህ የግብጽ ሠራዊት ሌሊቱን ሙሉ ወደ እስራኤላውያን መጠጋት አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ የምሥራቅ ነፋስ ባሕሩን ወደ ኋላ መለሰው፤ ነፋሱም ሌሊቱን ሙሉ በመንፈሱ፥ ባሕሩን ወደ ደረቅ ምድር ለወጠው፤ ውሃውም ከሁለት ተከፈለ፤
ዘፀአት 14:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እንዲመለሱና በሚግዶልና በባሕሩ መካከል፥ በበዓልጽፎንም ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ የእስራኤልን ልጆች ንገራቸው፤ ከእርሱም አንጻር በባህሩ ትሰፍራላችሁ።” ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ “በምድር ግራ በመጋባት ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው” ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያሳድዳቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም ማምለጣቸውን ለግብጽ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የአገልጋዮቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “ምንድነው ያደረግነው? እንዳያገለግለን እስራኤልን ለቀቅነው” አሉ። ሠረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችን፥ የግብጽንም ሰረገሎችን ሁሉ፥ የጦር አዛዦች በእያንዳንዱ ሠረገላ ላይ ነበሩ። ጌታም የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ በበዓልጽፎን ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ሰፍረው አገኙአቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን ከኋላቸው እየመጡ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ ጌታም ጮኹ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “በግብጽ መቃብር ስለ ሌለ ነው በምድረ በዳ እንድንሞት ያወጣኸን? ከግብጽ አውጥተህ ምንድነው ያደረግህብን? በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? ተወን፥ ግብፃውያንን እናገልግል፤ በምድረ በዳ ከምንሞት ብናገለግላቸው ይሻላልና።” ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የጌታን ማዳን እዩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና። ጌታ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ።