አስቴር 3:8-11
አስቴር 3:8-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህም ሃማን ለንጉሥ አርጤክስስ እንዲህ ሲል አስረዳው፦ “በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ውስጥ በየአገሩ ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች አሕዛብ የተለየ ሕግ አለው፤ ከዚህም በላይ ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ሕግ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ ታዲያ፥ ይህን ዐይነቱን ሕዝብ ዝም ብለህ ብትታገሥ ለአንተ አደገኛ ነገር ይሆንብሃል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህ ሕዝብ በሞት የሚቀጣበትን ዐዋጅ ለማስተላለፍ መልካም ፈቃድህ ይሁን፤ ይህን ብታደርግ እኔ ለንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ አስተዳደር መርጃ ይሆን ዘንድ ሦስት መቶ አርባ ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት ገቢ እንደማደርግ ቃል እገባለሁ።” ንጉሡም ዐዋጆችን ሁሉ ይፋ የሚያደርግበትን የቀለበት ማኅተም ወስዶ ለአጋጋዊው ለሃመዳታ ልጅ የአይሁድ ጠላት ለሆነው ለሃማን ሰጠው። ንጉሡም “እነሆ ሕዝቡ ከነንብረታቸው የአንተ ስለ ሆኑ በእነርሱ ላይ የወደድከውን አድርግ” ሲል ፈቀደለት።
አስቴር 3:8-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሐማ ንጉሥ ጠረክሲስን እንዲህ አለው፤ “በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አውራጃዎች ሁሉ ተሠራጭቶና ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ልማድ ያለውና የንጉሡንም ሕግ የማይታዘዝ ነው፤ ታዲያ ይህን ሕዝብ ዝም ማለቱ ለንጉሡ አይበጅም። ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ እነርሱን ለማጥፋት ዐዋጅ ይውጣ፤ እኔም ይህን ተግባር ለሚፈጽሙ ሰዎች የሚውል ዐሥር ሺሕ መክሊት ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት አስገባለሁ።” ስለዚህ ንጉሡ የቀለበት ማኅተሙን ከጣቱ አውልቆ የአይሁድ ጠላት ለሆነው ለአጋጋዊው ለሐማዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው። ንጉሡም ሐማን፣ “ገንዘቡን እዚያው ያዘው፤ ሕዝቡንም እንዳሻህ አድርገው” አለው።
አስቴር 3:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሐማም ንጉሡን አርጤክስስን፦ አንድ ሕዝብ በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አገሮች ሁሉ ተበትነዋል፥ ሕጋቸውም ከሕዝቡ ሁሉ ሕግ የተለየ ነው፥ የንጉሡንም ሕግ አይጠብቁም፥ ንጉሡም ይተዋቸው ዘንድ አይገባውም። ንጉሡም ቢፈቅድ እንዲጠፉ ይጻፍ፥ እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ያገቡት ዘንድ አሥር ሺህ መክሊት ብር የንጉሡን ሥራ በሚሠሩት እጅ እመዝናለሁ አለው። ንጉሡም ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ፥ ለአይሁድም ጠላት ለአጋጋዊው ለሐመዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው። ንጉሡም ሐማን፦ ደስ የሚያሰኝህን ነገር ታደርግባቸው ዘንድ ብሩም ሕዝቡም ለአንተ ተሰጥቶሃል አለው።