የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 3

3
1ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሡ አርጤክስስ የአጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፥ አከበረውም፥ ወንበሩንም ከእርሱ ጋር ከነበሩት አዛውንት ሁሉ በላይ አደረገለት። 2ንጉሡም ስለ እርሱ እንዲሁ አዝዞ ነበርና በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ ባሪያዎች ሁሉ ተደፍተው ለሐማ ይሰግዱ ነበር። መርዶክዮስ ግን አልተደፋም፥ አልሰገደለትም። 3በንጉሡም በር ያሉት የንጉሡ ባሪያዎች መርዶክዮስን፦ የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ? አሉት። 4ይህንም ዕለት ዕለት እየተናገሩ እርሱ ባልሰማቸው ጊዜ አይሁዳዊ እንደ ሆነ ነግሮአቸው ነበርና የመርዶክዮስ ነገር እንዴት እንደ ሆነ ያዩ ዘንድ ለሐማ ነገሩት። 5ሐማም መርዶክዮስ እንዳልተደፋለት እንዳልሰገደለትም ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 6የመርዶክዮስን ወገን ነግረውት ነበርና በመርዶክዮስ ብቻ እጁን ይጭን ዘንድ በዓይኑ ተናቀ፥ ሐማም በአርጤክስስ መንግሥት ሁሉ የነበሩትን የመርዶክዮስን ሕዝብ አይሁድን ሁሉ ሊያጠፋ ፈለገ።
7በንጉሡም በአርጤክስስ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከመጀመሪያው ወር ከኒሳን ጀምሮ በየዕለቱና በየወሩ እስከ አሥራ ሁለተኛው ወር እስከ አዳር ድረስ በሐማ ፊት ፉር የተባለውን ዕጣ ይጥሉ ነበር። 8ሐማም ንጉሡን አርጤክስስን፦ አንድ ሕዝብ በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አገሮች ሁሉ ተበትነዋል፥ ሕጋቸውም ከሕዝቡ ሁሉ ሕግ የተለየ ነው፥ የንጉሡንም ሕግ አይጠብቁም፥ ንጉሡም ይተዋቸው ዘንድ አይገባውም። 9ንጉሡም ቢፈቅድ እንዲጠፉ ይጻፍ፥ እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ያገቡት ዘንድ አሥር ሺህ መክሊት ብር የንጉሡን ሥራ በሚሠሩት እጅ እመዝናለሁ አለው። 10ንጉሡም ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ፥ ለአይሁድም ጠላት ለአጋጋዊው ለሐመዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው። 11ንጉሡም ሐማን፦ ደስ የሚያሰኝህን ነገር ታደርግባቸው ዘንድ ብሩም ሕዝቡም ለአንተ ተሰጥቶሃል አለው።
12በመጀመሪያውም ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፥ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ወዳሉ መቶ ሀያ ሰባት አገሮች፥ በየአገሩ ወዳሉ ሹማምትና አለቆች ወደ አሕዛብም ሁሉ ገዢዎች እንደ ቋንቋቸው በንጉሡ በአርጤክስስ ቃል ሐማ እንዳዘዘ ተጻፈ፥ በንጉሡም ቀለበት ታተመ። 13በአሥራ ሁለተኛው ወር በአዳር በአሥራ ሦስተኛው ቀን አይሁድን ሁሉ፥ ልጆችንና ሽማግሌዎችን፥ ሕፃናቶችንና ሴቶችን፥ በአንድ ቀን ያጠፉና ይገድሉ ዘንድ፥ ይደመስሱም ዘንድ፥ ምርኮአቸውንም ይዘርፉ ዘንድ ደብዳቤዎች በመልእክተኞች እጅ ወደ ንጉሡ አገሮች ሁሉ ተላኩ።
14በዚያም ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጅ በየአገሩ ላሉ አሕዛብ ሁሉ ታወጀ። 15መልእክተኞቹም በንጉሡ ትእዛዝ እየቸኰሉ ሄዱ፥ አዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ። ንጉሡና ሐማ ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ከተማይቱ ሱሳ ግን ተደናገጠች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ