የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 2

2
1ከዚህም ነገር በኋላ የንጉሡ የአርጤክስስ ቍጣ በበረደ ጊዜ አስጢንና ያደረገችውን የፈረደባትንም ነገር አሰበ። 2ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች እንዲህ አሉት፦ መልከ መልካም የሆኑ ደናግል ለንጉሡ ይፈለጉለት፥ 3ሴቶችን ከሚጠብቅ ከንጉሡ ጃንደረባ ከሄጌ እጅ በታች እንዲያደርጓቸው መልከ መልካሞቹን ደናግል ሁሉ ወደ ሱሳ ግንብ ወደ ሴቶች ቤት ይሰበስቡአቸው ዘንድ ንጉሡ በመንግሥቱ አገሮች ሁሉ ሹማምቶችን ያኑር፥ ቅባትና የሚያስፈልጋቸውም ይሰጣቸው፥ 4ንጉሡንም ደስ የምታሰኝ ቆንጆ በአስጢን ስፍራ ትንገሥ። ይህም ነገር ንጉሡን ደስ አሰኘው፥ እንዲሁም አደረገ።
5አንድ አይሁዳዊ የቂስ ልጅ የሰሜኢ ልጅ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል ብንያማዊ በሱሳ ግንብ ነበረ። 6እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከተማረኩት ምርኮኞች ጋር ከኢየሩሳሌም የተማረከ ነበረ። 7አባትና እናትም አልነበራትምና የአጎቱ ልጅ ሀደሳ የተባለችውን አስቴርን አሳድጎ ነበር፥ ቆንጆይቱም የተዋበችና መልከ መልካም ነበረች፥ አባትዋና እናትዋም ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ ወስዶአት ነበር።
8የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በተሰማ ጊዜ፥ ብዙም ቈነጃጅት ወደ ሱሳ ግንብ ወደ ሄጌ እጅ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ሴቶች ጠባቂው ወደ ሄጌ ተወሰደች። 9ቆንጆይቱም ደስ አሰኘችው፥ በእርሱም ዘንድ ሞገስ አገኘች፥ ቅባትዋንም ድርሻዋንም ከንጉሡም ቤት ልታገኝ የሚገባትን ሰባት ደንገጥሮች ፈጥኖ ሰጣት፥ እርስዋንና ደንገጥሮችዋንም በሴቶች ቤት በተመረጠ ስፍራ አኖረ። 10ይህንም እንዳትናገር መርዶክዮስ አዝዞአት ነበርና አስቴር ሕዝብዋንና ወገንዋን አልተናገረችም። 11መርዶክዮስም የአስቴርን ደኅንነትና የሚሆንላትን ያውቅ ዘንድ ዕለት ዕለት በሴቶች ቤት ወለል ትይዩ ይመላለስ ነበር።
12የመንጻታቸውም ወራት ስድስት ወር ያህል በከርቤ ዘይት፥ ስድስት ወርም በጣፋጭ ሽቱና በልዩ ልዩም በሚያነጻ ነገር ይፈጸም ነበርና እንደ ሴቶች ወግ አሥራ ሁለት ወር እንዲሁ ከተደረገላት በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ለመግባት የአንዳንዲቱ ቆንጆ ተራ በደረሰ ጊዜ፥ 13በዚህ ወግ ቆንጆይቱ ወደ ንጉሡ ትገባ ነበር፥ ከሴቶች ቤት ወደ ንጉሡ ቤት ለመውሰድ የምትሻውን ሁሉ ይሰጡአት ነበር። 14ማታም ትገባ ነበር፥ ሲነጋም ተመልሳ ወደ ሁለተኛው ሴቶች ቤት ቁባቶችን ወደሚጠብቅ ወደ ንጉሡ ጃንደረባ ወደ ጋይ ትመጣ ነበር፥ ንጉሡም ያልፈለጋት እንደ ሆነ፥ በስምዋም ያልተጠራች እንደሆነ፥ ከዚያ ወዲያ ወደ ንጉሡ አትገባም ነበር። 15ወደ ንጉሡም ትገባ ዘንድ የመርዶክዮስ አጎት የአቢካኢል ልጅ የአስቴር ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ጠባቂው የንጉሡ ጃንደረባ ሄጌ ከሚለው በቀር ምንም አልፈለገችም ነበር፥ አስቴርም በሚያዩአት ሁሉ ዓይን ሞገስ አግኝታ ነበርና።
16አርጤክስስም በነገሠ በሰባተኛው ዓመት አዳር በሚባለው በአሥራ ሁለተኛው ወር አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች። 17ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፥ በዓይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን አገኘች፥ የመንግሥቱንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ፥ በአስጢንም ፋንታ አነገሣት። 18ንጉሡም ስለ አስቴር ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ሰባት ቀን ያህል ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ ለአገሮቹም ሁሉ ይቅርታ አደረገ፥ እንደ ንጉሡም ለጋስነት መጠን ስጦታ ሰጠ።
19ደናግሉም ዳግመኛ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ይቀመጥ ነበር። 20አስቴርም ከእርሱ ጋር እንዳደገችበት ጊዜ የመርዶክዮስን ትእዛዝ ታደርግ ነበርና መርዶክዮስ እንዳዘዛት አስቴር ወገንዋንና ሕዝብዋን አልተናገረችም። 21በዚያም ወራት መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ ደጁን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ ተቈጡ፥ እጃቸውንም በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ ፈለጉ። 22ነገሩም ለመርዶክዮስ ተገለጠ፥ እርሱም ለንግሥቲቱ ለአስቴር ነገራት፥ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረች። 23ነገሩም ተመረመረ፥ እንዲህም ሆኖ ተገኘ፥ ሁለቱም በዛፍ ላይ ተሰቀሉ፥ ያም በንጉሡ ፊት በታሪክ መጽሐፍ ተጻፈ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ