ኤፌሶን 5:23-30
ኤፌሶን 5:23-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደ ሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና። ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ፥ እንዲሁም ሴቶች ለባሎቻቸው በሁሉ ይታዘዙ። ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት፥ ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደ ሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ። በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ፥ የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኵሰት እንዳያገኝባት፥ ቤተ ክርስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ፤ እንዲሁም ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው ይውደዱ፤ ሚስቱንም የወደደ ራሱን ወደደ። ከቶ ሥጋውን መጥላት የሚቻለው የለም፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ መገባት መግቡ፤ ጠብቁም። እኛ የአካሉ ሕዋሳት ነንና።
ኤፌሶን 5:23-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል። ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በቃሉ አማካይነት በውሃ ዐጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ እንዲሁም ጕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድድ ራሱን ይወድዳል። የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና።
ኤፌሶን 5:23-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል።
ኤፌሶን 5:23-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ባልም የሚስቱ ራስ ነው፤ ደግሞም ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን አዳኝዋ ነው። ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ እንዲሁም ሚስቶች በሁሉ ነገር ለባሎቻቸው ይታዘዙ። ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ክርስቶስ ይህን ያደረገው ቤተ ክርስቲያንን ሊቀድሳት ፈልጎ ነው፤ የቀደሳትም በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ ነው። በዚህ ዐይነት ዕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ መጥፎ ነገር ሳይገኝባት ቅድስት፥ እንከን የሌለባትና ውብ አድርጎ ወደራሱ ያቀርባታል። እንዲሁም ባሎች የገዛ ራሳቸውን እንደሚወዱ ሚስቶቻቸውን መውደድ ይገባቸዋል፤ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ራሱን አካል የሚጠላ ማንም የለም፤ ይልቅስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚያደርገው ዐይነት ራሱን ይመግባል፤ ይንከባከባልም። እኛም የክርስቶስ አካል ክፍሎች ነን፤
ኤፌሶን 5:23-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደሆነ ባል የሚስት ራስ ነው። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ እንደሰጣት፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ከውሃ መታጠብ ጋር በቃሉ አንጽቶ እንዲቀድሳት፥ እንዲሁም ጉድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር የሌለባት አድርጎ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ ሊያቀርባ እንደፈለገ፥ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ አካላቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የራሱን እካል የሚጠላ ከቶ የለምና፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበውማል። ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው እንዲህ ነው፤ ምክንያቱም እኛ የአካሉ ክፍሎች ነን።