ኤፌሶን 5:14-21
ኤፌሶን 5:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል። እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ። ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።
ኤፌሶን 5:14-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሎአልና። እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ። ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት። ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ። መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ። መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም። ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ። እግዚአብሔርን በመፍራት ለባልንጀሮቻችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።
ኤፌሶን 5:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።
ኤፌሶን 5:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በግልጥ የሚታይ ሁሉ ብርሃን ነው፤ ስለዚህ፦ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ! ከሙታን ተለይተህ ተነሥ! ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል። እንግዲህ እንዴት እንደምትኖሩ በጥንቃቄ አስተውሉ፤ እንደ ጥበበኞች እንጂ እንደ ሞኞች አትኑሩ። ይህ ዘመን ክፉ ስለ ሆነ በማናቸውም አጋጣሚ ጊዜ ተጠቀሙ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ወደ ጥፋት የሚመራችሁ ስለ ሆነ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይልቅስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊም ዜማ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በውዳሴና በመዝሙር በሙሉ ልባችሁ ጌታን አመስግኑ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር እግዚአብሔር አብን ዘወትር አመስግኑ። ለክርስቶስ ክብር ብላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ለሌላው ይታዘዝ።
ኤፌሶን 5:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። ስለዚህ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ፤ ከሙታንም ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል፤” ተብሏል። እንግዲህ ስለ አኗኗሯችሁ በጥንቃቄ ተጠበቁ፥ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው አይሁን፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ ብክነት እንደ ሆነው በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። እያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።