ኤፌሶን 2:11-18
ኤፌሶን 2:11-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የሆናችሁ፣ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፣ ራሳቸውን “ተገርዘናል” በሚሉት፣ “ያልተገረዙ” የተባላችሁ ያን አስታውሱ፤ በዚያን ዘመን ከክርስቶስ ተለይታችሁ፣ ከእስራኤል ወገንነት ርቃችሁ፣ ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን ሆናችሁ፣ በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል። ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤ ሕግንም፣ ከትእዛዞቹና ከሥርዐቱ ጋር በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው። ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ፤ ሁላችንም በእርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።
ኤፌሶን 2:11-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።
ኤፌሶን 2:11-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተ አሕዛብ አስቡ፤ ቀድሞ በሥጋ ሥርዐት ነበራችሁ፤ ያልተገዘሩም ይሉአችሁ ነበር፤ እንዲህ የሚሉአችሁም የተገዘሩ ሰዎች ናቸው፤ ግዝረት ግን በሥጋ ላይ የሚደረግ የሰው እጅ ሥራ ነው። ያንጊዜ ክርስቶስን አታውቁትም ነበር፤ ከእስራኤል ሕግ የተለያችሁ ነበራችሁ፤ ከተስፋው ሥርዐትም እንግዶች ነበራችሁ፤ ተስፋም አልነበራችሁም፤ በዚህም ዓለም እግዚአብሔርን አታውቁትም ነበር። አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ። ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና፥ በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ። ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በሥርዐቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ። በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ በእርሱም ጥልን አጠፋ። መጥቶም፤ ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን። እርሱ መርቶናልና፤ ሁለታችንንም በመንፈስ ቅዱስ ወደ አባቱ አቅርቦናልና።
ኤፌሶን 2:11-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልዳችሁ አሕዛብ የነበራችሁ፥ አይሁድ በሰው እጅ በመገረዛቸው እየተመኩ እናንተን ያልተገረዙ እያሉ ይሰድቡአችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። እናንተ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ግንኙነት የሌላችሁ፥ ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች የሆናችሁ፥ በዚህ ዓለምም አንዳች ተስፋ የሌላችሁ፥ ያለ እግዚአብሔር የምትኖሩ፥ ከክርስቶስም የተለያችሁ እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ከዚህ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በእርሱ ደም ቀርባችኋል። ለያይቶን የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰና አይሁድንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሰላማችን ክርስቶስ ነው። ከሁለቱ ሕዝቦች ከእርሱ ጋር የሚተባበር አንድ አዲስ ሕዝብን ለመፍጠር የሕግን ትእዛዞችና ደንቦች በሥጋው ሽሮ ሰላምን አደረገ። በመስቀል ላይ በመሞትም ጠላትነትን አስወገደ፤ ሁለቱንም አንድ አካል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቃቸው። መጥቶም ለእናንተ ርቃችሁ ለነበራችሁትና ቀርበው ለነበሩት ለአይሁድም የሰላምን የምሥራች ቃል ሰበከ። በእርሱ አማካይነት ሁላችንም በአንድ መንፈስ ተመርተን ወደ አብ እንቀርባለን።
ኤፌሶን 2:11-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፥ “ተገርዘናል” በሚሉት፥ “ያልተገረዛችሁ” የተባላችሁትን ያን አስታውሱ፤ በዚያ ዘመን በዚህም ዓለም ያለ ክርስቶስ ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ፥ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ፥ ተስፋን አጥታችሁና ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፥ ሁለቱን አንድ ያደረገ፥ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሕግን ከትእዛዛቱና ከሥርዓቱ ጋር ሻረ፤ ከሁለቱ አንድ አዲስ ሕዝብ ፈጥሮ ሰላምን አደረገ፤ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለቱን ሕዝቦች በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን ሰበከ፤ በእርሱም አማካኝነት ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት እንችላለን።