ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2
2
ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገር
1እናንተ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ምክንያት በመንፈሳዊ ኑሮአችሁ የሞታችሁ ነበራችሁ፤ 2በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ክፉ አካሄድ ትከተሉ ነበር፤ እንዲሁም በአየር ላይ ያሉትን የመናፍስት ኀይሎች ለሚገዛው ትታዘዙ ነበር፤ እርሱ በማይታዘዙት ሰዎች ላይ የሚሠራ ርኩሱ መንፈስ ነው። 3እኛም ሁላችን ከዚህ በፊት በእነርሱ መካከል የሥጋችንን ፈቃድና የአእምሮአችንን ሐሳብ እየተከተልን በሥጋችን ምኞት እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም በተፈጥሮአችን በእግዚአብሔር ቊጣ ሥር ነበርን።
4ነገር ግን የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ከመሆኑና ለእኛም ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ 5በበደላችን የሞትን ብንሆንም እንኳ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር እንድንኖር አድርጎናል፤ እናንተም የዳናችሁት በጸጋው ነው። #ቆላ. 2፥14። 6እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ አማካይነት ከእርሱው ጋር ከሞት አስነሥቶ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። 7ይህንንም ያደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የገለጠውን ቸርነትና ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና በሚመጡት ዘመናት ሊያሳየን ብሎ ነው። 8እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካይነት በጸጋው ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ በእናንተ ሥራ የተገኘ አይደለም። 9ማንም ሰው እንዳይመካ፥ የመዳን ጸጋ የተገኘው በሥራ አይደለም፤ 10እኛ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጃቸውን መልካም ሥራዎች እንድንሠራ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንደገና የተፈጠርን የእግዚአብሔር ፍጡሮች ነን።
በክርስቶስ የሚገኝ አንድነት
11ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልዳችሁ አሕዛብ የነበራችሁ፥ አይሁድ በሰው እጅ በመገረዛቸው እየተመኩ እናንተን ያልተገረዙ እያሉ ይሰድቡአችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። 12እናንተ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ግንኙነት የሌላችሁ፥ ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች የሆናችሁ፥ በዚህ ዓለምም አንዳች ተስፋ የሌላችሁ፥ ያለ እግዚአብሔር የምትኖሩ፥ ከክርስቶስም የተለያችሁ እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። 13አሁን ግን እናንተ ከዚህ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በእርሱ ደም ቀርባችኋል። 14ለያይቶን የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰና አይሁድንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሰላማችን ክርስቶስ ነው። 15ከሁለቱ ሕዝቦች ከእርሱ ጋር የሚተባበር አንድ አዲስ ሕዝብን ለመፍጠር የሕግን ትእዛዞችና ደንቦች በሥጋው ሽሮ ሰላምን አደረገ። 16በመስቀል ላይ በመሞትም ጠላትነትን አስወገደ፤ ሁለቱንም አንድ አካል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቃቸው። #ቆላ. 1፥20። 17መጥቶም ለእናንተ ርቃችሁ ለነበራችሁትና ቀርበው ለነበሩት ለአይሁድም የሰላምን የምሥራች ቃል ሰበከ። #ኢሳ. 57፥19። 18በእርሱ አማካይነት ሁላችንም በአንድ መንፈስ ተመርተን ወደ አብ እንቀርባለን።
19ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። 20በሐዋርያትና በነቢያትም መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 21ሕንጻው በሙሉ በእርሱ ተገጣጥሞ የጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል። 22እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚያድርበት ሕንጻ ለመሆን እናንተም አብራችሁ በክርስቶስ ትታነጻላችሁ።
Currently Selected:
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997