ኤፌሶን 1:15-21
ኤፌሶን 1:15-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህም እኔ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁን፥ ቅዱሳንንም ሁሉ መውደዳችሁን ሰምቼ፥ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ማመስገንንና በጸሎቴም እናንተን ማሰብን አላቋረጥሁም። ይኸውም የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር የጥበብን መንፈስ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ ዕውቀቱንም ይገልጽላችሁ ዘንድ፥ ዐይነ ልቡናችሁንም ያበራላችሁ ዘንድ፥ የተጠራችሁበት ተስፋም ምን እንደ ሆነ፥ በቅዱሳንም የርስቱ ክብር ባለጸግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ፥ በክርስቶስ እንደ አደረገው እንደ ከሃሊነቱ ታላቅነት በምናምን በእኛ ላይ የሚያደርገው የከሃሊነቱ ጽናት ብዛት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ ነው። ከሙታን ለይቶ ባስነሣው፥ በሰማይም በቀኙ ባስቀመጠው፥ ከመላእክት ሁሉ በላይ ከመኳንንትና ከኀይላት፥ ከአጋእዝትና ከሚጠራውም ስም ሁሉ በላይ፥ በዚህ ዓለም ብቻ አይደለም፤ በሚመጣውም ዓለም እንጂ።
ኤፌሶን 1:15-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነት፣ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንሥቶ፣ በጸሎቴ እያስታወስኋችሁ ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረብን አላቋረጥሁም። የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ። እንዲሁም በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኀይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየው ነው። የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፣ ከኀይልና ከጌትነት እንዲሁም በአሁኑ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ሊሰየም ከሚቻለው ስም ሁሉ በላይ ነው።
ኤፌሶን 1:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤
ኤፌሶን 1:15-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ በጌታ በኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምቼ እናንተን በጸሎቴ እያስታወስኩ በእናንተ ምክንያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረቤን አላቋርጥም። ክብር የሚገባው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔርን በይበልጥ ታውቁ ዘንድ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ። ለምን ዐይነት ተስፋ እንደ ተጠራችሁና ቅዱሳን የሚወርሱት ክቡር ርስት ምን ያኽል ብዙ እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልቡናችሁ ዐይን እንዲበራላችሁ እጸልያለሁ። የማይለካው ታላቅ ኀይሉ ለእኛ ለምናምነው ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ታውቁ ዘንድ እጸልያለሁ፤ ይህንንም ታላቅ ኀይሉን በተግባር ያሳየው ከሞት አስነሥቶ በሰማይ በቀኙ ባስቀመጠው በክርስቶስ አማካይነት ነው። እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን በሰማይ በቀኙ ያስቀመጠውም ከማንኛውም ግዛትና ሥልጣን ከኀይልና ጌትነት በላይ እንዲሁም በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ከስም ሁሉ በላይ የሆነውን ክቡር ስም በመስጠት ነው።
ኤፌሶን 1:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔ ደግሞ፥ በጌታ ኢየሱስ ለቅዱሳኖች ሁሉ ያላችሁን እምነትና ፍቅር ሰምቻለሁ፤ በዚህም ምክንያት፥ ስለ እናንተን በጸሎቴ ባስታወስኩ ቍጥር ምስጋናዬን አላቋረጥኩም። የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። በእርሱ የተጠራችሁበት ተስፋ ምን እንደሆን፥ ከቅዱሳንም ጋር የሚኖራችሁን የርስት ክብር ባለጠግነት ምንነት እንድታውቁ፥ የልቦናችሁ ዐይኖች እንዲበሩ፤ ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን፥ የኀይሉ ታላቅ ብርታት አሠራር፥ ኀይሉን ምን እንደሆን እንድታውቁ፥ ይህን ኃይል እርሱ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየ ነው። የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፥ ከኃይልና ከጌትነት እንዲሁም በዚህ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ ነው።