ዘዳግም 7:6-9
ዘዳግም 7:6-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ፥ ከአሕዛብ ሁሉ ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንት ከአሕዛብ ሁሉ ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ፥ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ፥ በተዘረጋችም ክንድ አወጣችሁ፤ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም፥ ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ ዕወቅ፤
ዘዳግም 7:6-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ። እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቍጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር። ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን ስለ ወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው። ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምላክ (ኤሎሂም) መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወድዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ (ኤሎሂም) ነው።
ዘዳግም 7:6-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ፤
ዘዳግም 7:6-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንተ እግዚአብሔር አምላክህ የራሱ ወገን አድርጎ የመረጠህ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ አንተ ለእርሱ የተለየህ ምርጥ ሕዝብ እንድትሆን አድርጎሃል። “እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ይበልጥ ብዙዎች በመሆናችሁ አይደለም፤ ይልቁንም እናንተ በምድር ላይ ከሁሉ በቊጥር ያነሳችሁ ሕዝብ ነበራችሁ። ነገር ግን እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደደ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የሰጠውን የተስፋ ቃል መጠበቅ ፈለገ፤ በታላቅ ኀይሉ ያዳናችሁና የግብጽ ንጉሥ ባርያዎች ከመሆን ነጻ ያወጣችሁም በዚህ ምክንያት ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፍጹም የታመነ አምላክ መሆኑን አስታውሱ፤ እርሱ ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል፤ ለሚወዱትና ትእዛዞቹንም ለሚፈጽሙ ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳያል።
ዘዳግም 7:6-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ለጌታ አምላክህ አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ፥ ጌታ አምላክህ ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ እንድትሆን መረጠህ። ጌታ የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፥ ይልቁንም እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁ፤ ነገር ግን ጌታ ስለ ወደዳችሁ፥ አባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አወጣችሁ። አንተም ጌታ አምላካችሁ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ፥ ለሚወዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደሆነ እወቅ፤