ኦሪት ዘዳግም 7
7
1አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጢያዊውን ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ 2አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በመታሃቸውም ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፤ 3ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። 4እንዳይከተለኝ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ የእግዚአብሔርም ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። 5ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። 6ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። 7እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ 8ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። 9አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ፤ 10የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፥ ነገር ግን በፊቱ ብድራት ይመልስበታል። 11እንግዲህ ታደርጋት ዘንድ እኔ ዛሬ ለአንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድንም ጠብቅ። 12እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤ 13ይወድድህማል፥ ይባርክህማል፥ ያበዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ የመሬትህንም ፍሬ፥ እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም፥ የከብትህንም ብዛት የበግህንም መንጋ ይባርክልሃል። 14ከአሕዛብም ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፤ በሰውህና በከብትህም ዘንድ ወንድ ቢሆን ወይም ሴት ብትሆን መካን አይሆንብህም። 15እግዚአብሔርም ሕማምን ሁሉ ከአንተ ያርቃል፤ የምታውቀውንም ክፉውን የግብፅ በሽታ ሁሉ በአንተ ላይ አያደርስብህም፥ በጠላቶችህም ሁሉ ላይ ያመጣባቸዋል። 16አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚጥላቸውን አሕዛብን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ፤ ዓይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ወጥመድ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው። 17በልብህም፦ እነዚህ አሕዛብ ከእኔ ይልቅ ይበዛሉና አወጣቸው ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብትል፥ አትፍራቸው፤ 18ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በፈረዖንና በግብፅ ሁሉ ያደረገውን፥ 19አምላክህ እግዚአብሔር፥ ዓይንህ እያየች፥ ታላቅን መቅሠፍት ምልክትንም ተአምራትንም የጸናችውን እጅ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፥ አስብ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። 20ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል። 21አምላክህ እግዚአብሔር፥ ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ፥ በመካከልህ ነውና ከእነርሱ የተነሣ አትደንግጥ። 22አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያወጣቸዋል፤ የምድረ በዳ አራዊት እንዳይበዙብህ አንድ ጊዜ ታጠፋቸው ዘንድ አይገባህም። 23አምላክህ እግዚአብሔር ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ድንጋጤ ያስደነግጣቸዋል። 24ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም በፊትህ ይቆም ዘንድ አይችልም። 25የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። 26እንደ እርሱም ርጉም እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፥ ጥላውም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ