ዘዳግም 7:1-6
ዘዳግም 7:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙና ታላላቅ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን፥ የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጤዎናዊውን፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ከነዓናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና በመታሃቸው ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፤ አትማራቸውም፤ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። ልጅህን ከእኔ ያርቀዋልና፤ ሌሎችን አማልክትም ያመልካልና። የእግዚአብሔርም ቍጣ ይነድድባችኋል፤ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የአማልክቶቻቸውንም ምስል በእሳት አቃጥሉ። “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና።
ዘዳግም 7:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፤ አትራራላቸውም። ከእነርሱ ጋራ ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤ ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላይህ ነድዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው። እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቍረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ። አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።
ዘዳግም 7:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጢያዊውን ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በመታሃቸውም ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፤ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። እንዳይከተለኝ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ የእግዚአብሔርም ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ።
ዘዳግም 7:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እግዚአብሔር አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህ ጊዜ በፊትህ ያሉትን ብዙ ሕዝቦች ያስወግድልሃል፤ እነርሱም ከአንተ በብዛትና በኀይል የሚበልጡት ሰባት የአሕዛብ ነገዶች ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። እግዚአብሔር አምላክህ እነዚህን ሁሉ ሕዝቦች ለእናንተ አሳልፎ ሲሰጣቸውና እነርሱን ድል በምትነሣበት ጊዜ ሁሉንም መደምሰስ አለብህ፤ ከእነርሱ ጋር ምንም ዐይነት ውል አታድርግ፤ አትራራላቸውም። ከእነርሱ አትጋባ፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆችህ ከእነርሱ ማንንም እንዲያገቡ አትፍቀድላቸው። ይህን ብታደርግ ልጆችህን ከእግዚአብሔር አስኰብልለው ባዕዳን አማልክትን እንዲከተሉ ያደርጉአቸዋል፤ ይህም ከሆነ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ተቈጥቶ ወዲያው ያጠፋሃል፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ የምታደርጉት እንደዚህ ነው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ ከድንጋይ የተሠሩ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም እያንከታከታችሁ ጣሉ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሰባብሩ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላክህ የራሱ ወገን አድርጎ የመረጠህ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ አንተ ለእርሱ የተለየህ ምርጥ ሕዝብ እንድትሆን አድርጎሃል።
ዘዳግም 7:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ጌታ አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከአንተ የበለጡትን እና የበረቱትን ሰባቱን አሕዛብ፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን ባስወጣልህ ጊዜ፥ ጌታ አምላክህም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና ድል በምትነሣበት ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፥ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፥ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፥ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ፤ እኔን እንዳይከተል፥ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ ያኔ የጌታ ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም አድቅቁት፥ የእነርሱንም አሼራ ሰባብሩ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። “ለጌታ አምላክህ አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ፥ ጌታ አምላክህ ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ እንድትሆን መረጠህ።