ዘዳግም 7:1-26

ዘዳግም 7:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልት​ወ​ር​ሳት ወደ​ም​ት​ገ​ባ​ባት ምድር ባመ​ጣህ ጊዜ፥ ከፊ​ት​ህም ብዙና ታላ​ላቅ አሕ​ዛ​ብን፥ ከአ​ንተ የበ​ለ​ጡ​ትን፥ የበ​ረ​ቱ​ት​ንም ሰባ​ቱን አሕ​ዛብ፥ ኬጤ​ዎ​ና​ዊ​ውን፥ ጌር​ጌ​ሴ​ዎ​ና​ዊ​ው​ንም፥ አሞ​ሬ​ዎ​ና​ዊ​ው​ንም፥ ከነ​ዓ​ና​ዊ​ው​ንም፥ ፌር​ዜ​ዎ​ና​ዊ​ው​ንም፥ ኤዌ​ዎ​ና​ዊ​ው​ንም፥ ኢያ​ቡ​ሴ​ዎ​ና​ዊ​ው​ንም ባወጣ ጊዜ፥ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ጅህ አሳ​ልፎ በሰ​ጣ​ቸ​ውና በመ​ታ​ሃ​ቸው ጊዜ፥ ፈጽ​መህ አጥ​ፋ​ቸው፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ቃል ኪዳን አታ​ድ​ርግ፤ አት​ማ​ራ​ቸ​ውም፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር አት​ጋባ፤ ሴት ልጅ​ህን ለወ​ንድ ልጁ አት​ስጥ፥ ሴት ልጁ​ንም ለወ​ንድ ልጅህ አት​ው​ሰድ። ልጅ​ህን ከእኔ ያር​ቀ​ዋ​ልና፤ ሌሎ​ችን አማ​ል​ክ​ትም ያመ​ል​ካ​ልና። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቍጣ ይነ​ድ​ድ​ባ​ች​ኋል፤ ፈጥ​ኖም ያጠ​ፋ​ች​ኋል። ነገር ግን እን​ዲህ አድ​ር​ጉ​ባ​ቸው፤ መሠ​ዊ​ያ​ቸ​ውን አፍ​ርሱ፤ ሐው​ል​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ሰባ​ብሩ፥ የማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀ​ዶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ቍረጡ፥ የአ​ማ​ል​ክ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ምስል በእ​ሳት አቃ​ጥሉ። “ለአ​ም​ላ​ክህ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በም​ድር ፊት ከሚ​ኖሩ አሕ​ዛብ ሁሉ ይልቅ ለእ​ርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆ​ን​ለት ዘንድ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መር​ጦ​ሃ​ልና። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የወ​ደ​ዳ​ች​ሁና የመ​ረ​ጣ​ችሁ፥ ከአ​ሕ​ዛብ ሁሉ ስለ በዛ​ችሁ አይ​ደ​ለም፤ እና​ንት ከአ​ሕ​ዛብ ሁሉ ጥቂ​ቶች ነበ​ራ​ች​ሁና፤ ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ ወደ​ዳ​ችሁ፥ ለአ​ባ​ቶ​ቻ​ች​ሁም የማ​ለ​ላ​ቸ​ውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለ​ዚህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጽኑ እጅ፥ በተ​ዘ​ረ​ጋ​ችም ክንድ አወ​ጣ​ችሁ፤ ከባ​ር​ነ​ትም ቤት ከግ​ብፅ ንጉሥ ከፈ​ር​ዖን እጅ አዳ​ና​ችሁ። አን​ተም አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እርሱ አም​ላክ እንደ ሆነ፥ ለሚ​ወ​ድ​ዱ​ትም፥ ትእ​ዛ​ዙ​ንም ለሚ​ጠ​ብቁ ቃል ኪዳ​ኑ​ንና ምሕ​ረ​ቱን እስከ ሺህ ትው​ልድ ድረስ የሚ​ጠ​ብቅ የታ​መነ አም​ላክ እንደ ሆነ ዕወቅ፤ የሚ​ጠ​ሉ​ትን ለማ​ጥ​ፋት በፊ​ታ​ቸው ብድ​ራት ይመ​ል​ስ​ባ​ቸ​ዋል፤ ለሚ​ጠ​ላው አይ​ዘ​ገ​ይም፤ ነገር ግን በፊቱ ብድ​ራ​ትን ይመ​ል​ስ​በ​ታል። እን​ግ​ዲህ ታደ​ር​ጓት ዘንድ እኔ ዛሬ ለእ​ና​ንተ የማ​ዝ​ዛ​ትን ትእ​ዛ​ዝና ሥር​ዐት፥ ፍር​ድ​ንም ጠብቁ። “እን​ዲ​ህም ይሆ​ናል፤ ይህ​ችን ፍርድ ሰም​ታ​ችሁ ብት​ጠ​ብ​ቋት፥ ብታ​ደ​ር​ጓ​ትም፥ አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለአ​ባ​ቶ​ቻ​ችሁ የማ​ለ​ውን ቃል ኪዳ​ንና ምሕ​ረት ለእ​ና​ንተ ይጠ​ብ​ቅ​ላ​ች​ኋል፤ ይወ​ድ​ድ​ህ​ማል፤ ይባ​ር​ክ​ህ​ማል፤ ያባ​ዛ​ህ​ማል፤ ይሰ​ጥ​ህም ዘንድ ለአ​ባ​ቶ​ችህ በማ​ለ​ላ​ቸው ምድር የሆ​ድ​ህን ፍሬ፥ የመ​ሬ​ት​ህ​ንም ፍሬ፥ እህ​ል​ህን፥ ወይ​ን​ህ​ንም፥ ዘይ​ት​ህ​ንም፥ የከ​ብ​ት​ህ​ንም ብዛት፥ የበ​ግ​ህ​ንም መንጋ ይባ​ር​ክ​ል​ሃል። ከአ​ሕ​ዛ​ብም ሁሉ ይልቅ የተ​ባ​ረ​ክህ ትሆ​ና​ለህ፤ ከሴ​ቶ​ችህ መካን አት​ኖ​ርም፤ ልጆች የሌ​ሏት አገ​ል​ጋ​ይም አት​ኖ​ርም፤ ከከ​ብ​ት​ህም መካን አይ​ኖ​ርም። በግ​ብ​ፃ​ው​ያን ላይ ሲመጣ ያየ​ኸ​ውን ክፉ ሕማ​ምና ደዌ ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ያር​ቅ​ል​ሃል፤ ያየ​ኸ​ው​ንም መከራ ሁሉ ወደ አንተ አያ​መ​ጣ​ውም፤ ከአ​ን​ተም በሚ​ጠ​ሉህ ሁሉ ላይ ይመ​ል​ሰ​ዋል። አም​ላ​ክ​ህም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሚ​ሰ​ጥ​ህን የአ​ሕ​ዛብ ምርኮ ትበ​ላ​ለህ፤ ዐይ​ን​ህም አታ​ዝ​ን​ላ​ቸ​ውም፤ ያም ለአ​ንተ ክፉ ይሆ​ን​ብ​ሃ​ልና አማ​ል​ክ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን አታ​ም​ል​ካ​ቸው። “በል​ብ​ህም፦ እነ​ዚህ አሕ​ዛብ ከእኔ ይልቅ ይበ​ዛ​ሉና አወ​ጣ​ቸው ዘንድ እን​ዴት እች​ላ​ለሁ? ብለህ፥ አት​ፍ​ራ​ቸው፤ ነገር ግን አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በፈ​ር​ዖ​ንና በግ​ብ​ፃ​ው​ያን ሁሉ ያደ​ረ​ገ​ውን ፈጽ​መህ አስብ፤ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዓይ​ንህ እያ​የች፥ ታላቅ መቅ​ሠ​ፍ​ትን፥ ምል​ክ​ት​ንም፥ ተአ​ም​ራ​ት​ንም፥ የጸ​ና​ች​ው​ንም እጅ፥ የተ​ዘ​ረ​ጋ​ው​ንም ክንድ አድ​ርጎ እን​ዳ​ወ​ጣህ፤ እን​ዲሁ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አንተ በም​ት​ፈ​ራ​ቸው በአ​ሕ​ዛብ ሁሉ ላይ ያደ​ር​ጋል። ደግ​ሞም አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የቀ​ሩት፥ ከፊ​ት​ህም የተ​ሸ​ሸ​ጉት እስ​ኪ​ጠፉ ድረስ መቅ​ሠ​ፍ​ትን ይል​ክ​ባ​ቸ​ዋል። ከፊ​ታ​ቸው አት​ደ​ን​ግጥ፤ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ ከአ​ንተ ጋር ነውና፥ እር​ሱም አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታላ​ቅና ጽኑዕ ነውና። አም​ላ​ክ​ህም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እነ​ዚ​ህን አሕ​ዛብ በጥ​ቂት በጥ​ቂቱ ከፊ​ትህ ያጠ​ፋ​ቸ​ዋል፤ ምድ​ርም ምድረ በዳ እን​ዳ​ት​ሆን የም​ድረ በዳ አራ​ዊ​ትም እን​ዳ​ይ​በ​ዙ​ብህ ፈጥኜ አጠ​ፋ​ቸ​ዋ​ለሁ አት​በል። አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን እነ​ር​ሱን በእ​ጅህ አሳ​ልፎ ይሰ​ጣ​ቸ​ዋል፥ እስ​ኪ​ጠ​ፉም ድረስ በታ​ላቅ ውር​ደት ይደ​መ​ስ​ሳ​ቸ​ዋል። ነገ​ሥ​ታ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም በእ​ጅህ አሳ​ልፎ ይሰ​ጣ​ቸ​ዋል፤ ስማ​ቸ​ው​ንም ከዚያ ቦታ ያጠ​ፋል፤ እስ​ክ​ታ​ጠ​ፋ​ቸው ድረስ ማንም ከፊ​ትህ ይቆም ዘንድ አይ​ች​ልም። የአ​ም​ላ​ኮ​ቻ​ቸ​ውን ምስል በእ​ሳት ታቃ​ጥ​ላ​ለህ፤ ከእ​ነ​ር​ሱም የተ​ሠ​ራ​ባ​ቸ​ውን ብር​ንና ወር​ቅን፥ አት​መኝ፤ በአ​ም​ላ​ክ​ህም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እን​ዳ​ት​በ​ድ​ል​በት ከእ​ርሱ ምንም አት​ው​ሰድ። ርኩ​ስን ነገር ወደ ቤትህ አታ​ግባ፤ እንደ እር​ሱም ርጉም ትሆ​ና​ለህ፤ ርጉም ነውና መጸ​የ​ፍን ተጸ​የ​ፈው፤ መጥ​ላ​ት​ንም ጥላው።

ዘዳግም 7:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፤ አትራራላቸውም። ከእነርሱ ጋራ ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤ ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላይህ ነድዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው። እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቍረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ። አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ። እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቍጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር። ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው። ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወድዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ ነው። ነገር ግን፣ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ይበቀላቸዋል፤ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ለመበቀል አይዘገይም። ስለዚህ በዛሬው ቀን የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ለመከተል ጥንቃቄ አድርግ። እነዚህን ሕግጋት ብታዳምጥና በጥንቃቄ ብትጠብቃቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ከአንተ ጋራ የገባውን የፍቅር ኪዳኑን ይጠብቃል። ይወድድሃል፤ ይባርክሃል፤ ያበዛሃልም። ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የማሕፀንህን ፍሬ፣ የምድርህን ሰብል፣ እህልህን፣ አዲሱን ወይንና ዘይት፤ የከብት መንጋህን ጥጆች፣ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገሎች ይባርካል። ከሕዝቦች ሁሉ የበለጠ አንተ ትባረካለህ፤ ከአንተ ወይም ከከብቶችህ መካከል የማይወልድ ወንድ ወይም ሴት አይኖርም። እግዚአብሔር ከማናቸውም በሽታ ነጻ ያደርግሃል፤ በግብጽ የምታውቃቸውን እነዚያን አሠቃቂ በሽታዎች በሚጠሉህ ሁሉ ላይ እንጂ በአንተ ላይ አያመጣብህም። አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ። “እነዚህ አሕዛብ ከእኛ ይልቅ ጠንካሮች ስለ ሆኑ፣ እንዴት አድርገን እናስወጣቸዋለን?” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል። ነገር ግን አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብጽ ሁሉ ላይ ያደረገውን በሚገባ አስታውስ። ታላላቅ ፈተናዎችን፣ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን አምላክህ እግዚአብሔር አንተን ያወጣበትን ብርቱ እጅና የተዘረጋች ክንድ በገዛ ዐይንህ አይተሃል። አምላክህ እግዚአብሔር አሁን በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያንኑ ያደርጋል። ይልቁንም አምላክህ እግዚአብሔር በሕይወት ተርፈው፣ ከአንተ የተደበቁት እንኳ እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ተርብ ይሰድድባቸዋል። በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ ስለ ሆነ አያስደንግጡህ። አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊቱ ቍጥር በአካባቢህ እንዳይበራከት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይፈቀድልህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ግን እስኪጠፉ ድረስ ከባድ ትርምስ ፈጥሮባቸው በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል። ነገሥታታቸውን በእጅህ ይጥላቸዋል፤ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ። እስክትደመስሳቸው ድረስ አንተን መቋቋም የሚችል አንድም ሰው የለም። የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል። አስጸያፊ ነገርን ወደ ቤትህ ወይም ወደ ራስህ አታምጣ፤ አለዚያ አንተም እንደ እርሱ ለጥፋት ትዳረጋለህ፤ ፈጽመህ ጥላው፤ ተጸየፈውም፤ ለጥፋት የተለየ ነውና።

ዘዳግም 7:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጢያዊውን ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በመታሃቸውም ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፤ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። እንዳይከተለኝ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ የእግዚአብሔርም ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ፤ የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፥ ነገር ግን በፊቱ ብድራት ይመልስበታል። እንግዲህ ታደርጋት ዘንድ እኔ ዛሬ ለአንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድንም ጠብቅ። እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤ ይወድድህማል፥ ይባርክህማል፥ ያበዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ የመሬትህንም ፍሬ፥ እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም፥ የከብትህንም ብዛት የበግህንም መንጋ ይባርክልሃል። ከአሕዛብም ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፤ በሰውህና በከብትህም ዘንድ ወንድ ቢሆን ወይም ሴት ብትሆን መካን አይሆንብህም። እግዚአብሔርም ሕማምን ሁሉ ከአንተ ያርቃል፤ የምታውቀውንም ክፉውን የግብፅ በሽታ ሁሉ በአንተ ላይ አያደርስብህም፥ በጠላቶችህም ሁሉ ላይ ያመጣባቸዋል። አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚጥላቸውን አሕዛብን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ፤ ዓይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ወጥመድ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው። በልብህም፦ እነዚህ አሕዛብ ከእኔ ይልቅ ይበዛሉና አወጣቸው ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብትል፥ አትፍራቸው፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በፈረዖንና በግብፅ ሁሉ ያደረገውን፥ አምላክህ እግዚአብሔር፥ ዓይንህ እያየች፥ ታላቅን መቅሠፍት ምልክትንም ተአምራትንም የጸናችውን እጅ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፥ አስብ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል። አምላክህ እግዚአብሔር፥ ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ፥ በመካከልህ ነውና ከእነርሱ የተነሣ አትደንግጥ። አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያወጣቸዋል፤ የምድረ በዳ አራዊት እንዳይበዙብህ አንድ ጊዜ ታጠፋቸው ዘንድ አይገባህም። አምላክህ እግዚአብሔር ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ድንጋጤ ያስደነግጣቸዋል። ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም በፊትህ ይቆም ዘንድ አይችልም። የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። እንደ እርሱም ርጉም እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፥ ጥላውም።

ዘዳግም 7:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“እግዚአብሔር አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህ ጊዜ በፊትህ ያሉትን ብዙ ሕዝቦች ያስወግድልሃል፤ እነርሱም ከአንተ በብዛትና በኀይል የሚበልጡት ሰባት የአሕዛብ ነገዶች ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። እግዚአብሔር አምላክህ እነዚህን ሁሉ ሕዝቦች ለእናንተ አሳልፎ ሲሰጣቸውና እነርሱን ድል በምትነሣበት ጊዜ ሁሉንም መደምሰስ አለብህ፤ ከእነርሱ ጋር ምንም ዐይነት ውል አታድርግ፤ አትራራላቸውም። ከእነርሱ አትጋባ፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆችህ ከእነርሱ ማንንም እንዲያገቡ አትፍቀድላቸው። ይህን ብታደርግ ልጆችህን ከእግዚአብሔር አስኰብልለው ባዕዳን አማልክትን እንዲከተሉ ያደርጉአቸዋል፤ ይህም ከሆነ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ተቈጥቶ ወዲያው ያጠፋሃል፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ የምታደርጉት እንደዚህ ነው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ ከድንጋይ የተሠሩ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም እያንከታከታችሁ ጣሉ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሰባብሩ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላክህ የራሱ ወገን አድርጎ የመረጠህ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ አንተ ለእርሱ የተለየህ ምርጥ ሕዝብ እንድትሆን አድርጎሃል። “እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ይበልጥ ብዙዎች በመሆናችሁ አይደለም፤ ይልቁንም እናንተ በምድር ላይ ከሁሉ በቊጥር ያነሳችሁ ሕዝብ ነበራችሁ። ነገር ግን እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደደ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የሰጠውን የተስፋ ቃል መጠበቅ ፈለገ፤ በታላቅ ኀይሉ ያዳናችሁና የግብጽ ንጉሥ ባርያዎች ከመሆን ነጻ ያወጣችሁም በዚህ ምክንያት ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፍጹም የታመነ አምላክ መሆኑን አስታውሱ፤ እርሱ ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል፤ ለሚወዱትና ትእዛዞቹንም ለሚፈጽሙ ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳያል። ነገር ግን የሚጠሉትን በማጥፋት ይበቀላል፤ እነርሱንም ከመበቀል ፈጽሞ አይዘገይም። ስለዚህም ዛሬ እኔ ያዘዝኩህን ትእዛዝ፥ ሕግና ሥርዓት በጥንቃቄ ጠብቅ። “እነዚህን ትእዛዞች ብታዳምጥና በታማኝነትም ብትፈጽማቸው፥ እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ በመሐላ የሰጠውን ቃል ኪዳንና ዘለዓለማዊ ፍቅር ለአንተም ያጸናልሃል፤ እርሱ አንተን ይወድሃል፤ ይባርክህማል፤ ስለዚህም በቊጥር ትበዛለህ፤ የምትወልዳቸው ልጆች ይባረካሉ፤ የምድርህም ፍሬ ይባረካል፤ ስለዚህም ብዙ እህል፥ ወይንና የወይራ ዘይት ታገኛለህ፤ ከዚህም ጋር ብዙ የከብትና የበግ መንጋ ያበዛልሃል፤ ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ ተስፋ በሰጠው ምድር ላይ ይህን ሁሉ በረከት ይሰጥሃል። የአንተን ያኽል በብዙ የተባረከ ሕዝብ በዓለም ላይ ከቶ አይገኝም፤ ከአንተ መካከል ወንድም ሆነ ሴት እንዲሁም ከእንስሶችህ መካከል መኻን አይገኝም። እግዚአብሔር ከበሽታ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ በግብጽ አገር በነበርክ ጊዜ ካየኸው አሠቃቂ በሽታ ሁሉ ማንኛውንም በአንተ ላይ አያመጣም፤ ነገር ግን እነዚህን በሽታዎች በሚጠሉህ ላይ ያመጣባቸዋል። እግዚአብሔር በእጅህ ላይ የጣለልህን ሕዝቦች ሁሉ ያለ ርኅራኄ ደምስስ፤ ጣዖቶቻቸውንም ለማምለክ ወጥመድ ውስጥ አትግባ። “ ‘እነዚህ ሕዝቦች ከእኔ ይበልጣሉ፤ እንዴትስ አድርጌ እነርሱን ነቅዬ አወጣቸዋለሁ’ ብለህ በማሰብ አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ያደረገውን አስታውስ። በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን ታላላቅ መቅሠፍቶች፥ ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክህ አንተን ነጻ ያወጣበትን ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን አስታውስ፤ ግብጻውያንን ባጠፋበት ዐይነት ዛሬ አንተ የምትፈራቸውን እነዚህንም ሕዝቦች ሁሉ ያጠፋቸዋል። አምላክህ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ሽብር እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ከአንተ ሸሽተው የተደበቁት እንኳ ይጠፋሉ። ስለዚህም እነዚህን ሕዝቦች አትፍራ፤ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነው፤ እርሱ ታላቅና መፈራትም የሚገባው አምላክ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት እየነቃቀለ ያስወጣቸዋል፤ እነርሱን ሁሉ በአንድ ጊዜ ማጥፋት አትችልም፤ ይህን ብታደርግ አራዊት በምድሪቱ ላይ በዝተው ያስቸግሩሃል፤ እግዚአብሔር ጠላቶችህን በእጆችህ ላይ ይጥልልሃል፤ እስኪደመሰሱም ድረስ በብርቱ ያሸብራቸዋል፤ ንጉሦቻቸውን በእጅህ ይጥልልሃል፤ እነርሱንም ታጠፋና ስማቸው የተረሳ እንዲሆን ታደርጋለህ፤ ማንም ተቋቊሞ ሊገታህ አይችልም፤ ሁሉንም ታወድማለህ። ጣዖቶቻቸውን በእሳት አቃጥል፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ የራስህ ንብረት አድርገህ ለመውሰድ ልብህ አይመኝ፤ ይህን ብታደርግ ወጥመድ ይሆንብሃል፤ እግዚአብሔርም አምልኮ ጣዖትን ስለሚጠላ ብርቱ ጥፋትን ያስከትልብሃል። እነዚህንም የረከሱ ጣዖቶች ወደ ቤትህ አታስገባ፤ ብታስገባ ግን አንተም እንደ እነርሱ ትጠፋለህ፤ እነርሱ ለጥፋት የተገቡ ስለ ሆነ በጣም ልትጠላቸውና ልትጸየፋቸው ይገባል።

ዘዳግም 7:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“ጌታ አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከአንተ የበለጡትን እና የበረቱትን ሰባቱን አሕዛብ፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን ባስወጣልህ ጊዜ፥ ጌታ አምላክህም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና ድል በምትነሣበት ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፥ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፥ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፥ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ፤ እኔን እንዳይከተል፥ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ ያኔ የጌታ ቁጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም አድቅቁት፥ የእነርሱንም አሼራ ሰባብሩ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። “ለጌታ አምላክህ አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ፥ ጌታ አምላክህ ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ እንድትሆን መረጠህ። ጌታ የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፥ ይልቁንም እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁ፤ ነገር ግን ጌታ ስለ ወደዳችሁ፥ አባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አወጣችሁ። አንተም ጌታ አምላካችሁ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ፥ ለሚወዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደሆነ እወቅ፤ የሚጠሉትን በማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፥ ለሚጠላው አይዘገይም፥ በፊቱ ብድራት ይመልስበታል። እንግዲህ እንድታደርገው ዛሬ ያዘዝኩህን ትእዛዝ፥ ሥርዓትና ፍርድ በጥንቃቄ ጠብቅ። “እንዲህም ይሆናል፥ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ጌታ አምላካችሁ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ዘላለማዊ ፍቅር ለአንተም ይጠብቅልሃል፥ ይወድድህማል፥ ይባርክህማል፥ ያበዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ እንዲሁም የምድርህንም ፍሬ፥ እህልና ወይንህን፥ ዘይትህንም፥ በከብትም ብዛት በበግም መንጋ አብዝቶ ይባርክልሃል። ከሕዝቦች ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፥ ወንድ ይሁን ወይም ሴት በሰውህና በከብትህም ዘንድ መካን አይኖርብህም። ጌታም ሕማምን ሁሉ ከአንተ ያርቃል፥ የምታውቀውንም ክፉውን የግብጽ በሽታ ሁሉ በአንተ ላይ አያደርስብህም፥ በሚጠሉህ ሁሉ ላይ ግን ያመጣባቸዋል። ጌታ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ የሚጥላቸውን ሕዝቦች ሁሉ ታጠፋቸዋለህ፥ ዓይንህም አታዝንላቸውም፤ ወጥመድ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው። “በልብህም፦ ‘እነዚህ ሕዝቦች ከእኔ ይበልጣሉ፤ እንዴትስ አድርጌ አስወጣቸዋለሁ?’ ብለህ፥ ልትፈራቸው አይገባም፥ ነገር ግን ጌታ አምላካችሁ በፈረዖንና በግብጽ ሁሉ ያደረገውን አስብ፥ ዓይንህ ያየችውን ታላቅን መቅሠፍት፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ ጌታ አምላክህ ሲያስወጣህ የጸናችውን እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ፥ እንደዚሁ ሁሉ ጌታ አምላክህ አንተ በምትፈራቸው በሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደርጋል። ደግሞም ጌታ አምላካችሁ የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል። ጌታ አምላክህ፥ ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ፥ በመካከልህ ነውና በእነርሱ የተነሣ ልትደናገጥ አይገባም። ጌታ አምላካችሁ እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊት እንዳይበዙብህ፥ እነርሱን በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይቻልህም። ጌታ አምላካችሁ ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ሁከት ላይ ይጥላቸዋል። ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም ተቋቁሞህ በፊት ሊቆም አይችልም። የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ አትመኝ፥ በጌታ አምላካችሁም ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። እንደ እርሱም ለጥፋት የምትሆን እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፥ ጥላውም።