ዘዳግም 18:9-14
ዘዳግም 18:9-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም፥ በወፍም የሚያሟርት በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያጠፋቸዋል። አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን። አንተ የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ ለአንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ አምላክህ እግዚአብሔር አልፈቀደምና።
ዘዳግም 18:9-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፣ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል። በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፣ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ ነውና። ከእነዚህ አስጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል። በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ነውር አልባ ሁን። ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፣ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አልፈቀደልህም።
ዘዳግም 18:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኩሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቁልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቍይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኩሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል። አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን። የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከልክሎሃል።
ዘዳግም 18:9-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚፈጽሙትን አጸያፊ ልማድ ሁሉ አትከተል። ማንም ከመካከልህ ወንድ ልጁን፥ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ አይኑር፤ ወይም አስማተኛ፥ ሟርተኛ፥ ጠንቋይ፥ መተተኛ አይሁን። ወይም ደግሞ መናፍስትን የሚጠራ ወይም ከመናፍስት ጋር የሚነጋገር፥ ወይም የሙታን መናፍስትን የሚስብ አይኑር። ይህን የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላና አጸያፊ ነው፤ አንተ ወደ ፊት በተራመድህ ቊጥር አምላክህ እግዚአብሔር አሕዛብን ከፊትህ ነቃቅሎ የሚያሳድድበት ምክንያት ይህንኑ ዐይነት የረከሰ ሥራ በማድረጋቸው ነው። አንተ ግን ለእግዚአብሔር በፍጹም ታማኝ መሆን ይገባሃል።” ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሀገራቸውን አስለቅቀህ የምትወርስባቸው ሕዝቦች ሟርተኝነትንና ጥንቈላን ይወዳሉ፤ አንተ ግን እግዚአብሔር አምላክህ ይህን እንድታደርግ አይፈቅድም።
ዘዳግም 18:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“አምላክህ ጌታ ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፥ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል። በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ፥ ወይም መተተኛ፥ ሞራ ገለጭ፥ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቁል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነውና፥ ከእነዚህ አጸያፊ ልምዶች የተነሣም ጌታ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል። በአምላክህ በጌታ ፊት ነውር አልባ ሁን።” ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፥ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ ጌታ እግዚአብሔር አልፈቀደልህም።