ዘዳግም 11:16-25
ዘዳግም 11:16-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም ተጠንቀቁ። የእግዚአብሔርም ቍጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ፥ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፥ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ። “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፤ በዐይኖቻችሁም መካከል እንደማይንቀሳቀስ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፤ በቤትም ሲቀመጡ፥ በመንገድም ሲሄዱ፥ ሲተኙም፥ ሲነሡም እንዲነጋገሩበት፤ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። በምድር ላይ የሰማይን ዘመን ያህል ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ እርሱንም ትከተሉ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ ብታደርጉአትም፥ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፤ ከእናንተም የሚበልጡትን፥ የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ። የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም፥ ከአንጢሊባኖስም፥ ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን፥ ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል።
ዘዳግም 11:16-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ተታልላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም። ከዚያም የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ እርሱም ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ። እነዚህን ቃሎቼን፣ በልባችሁና በአእምሯችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፣ በግንባራችሁም ላይ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር። በቤትህ መቃኖችና በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ፣ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፣ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከርሱም ጋራ ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፣ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ። በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተምዕራብ እስካለው ባሕር ይደርሳል። ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።
ዘዳግም 11:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም፥ የእግዚአብሔርም ቁጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፤ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ። እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፥ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው። እርስዋንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር፥ እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ፥ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ ብታደርጉአትም፥ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፥ ከእናንተም የሚበልጡትን የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ። የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም ከሊባኖስም ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል።
ዘዳግም 11:16-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ባዕዳን አማልክትን ለመከተልና ለማምለክ ዘወር እንዳትሉ ተጠንቀቁ። ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይቈጣል፤ ሰማያትን ዘግቶ ምድሪቱን ዝናብ እንዳይዘንብባትና ፍሬ እንዳትሰጥ ያደርጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር ከሚሰጣችሁ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ። “እነዚህን ትእዛዞች ዘወትር በልቡናችሁና በአእምሮአችሁ ቅረጹአቸው፤ መታሰቢያም ይሆኑላችሁ ዘንድ እነርሱን በክንዳችሁ ላይ እሰሩ፤ በግንባራችሁም ላይ እንደማስታወሻ አኑሩአቸው፤ ለልጆቻችሁም አስተምሩአቸው፤ በቤት በምትቀመጡበት ጊዜ፥ ወይም ስትሄዱ፥ ዕረፍት በምታደርጉበትም ሆነ በምትሠሩበት ጊዜ ሁሉ ስለ እነርሱ ተነጋገሩ፤ በቤትህ የበር መቃኖችና በቅጽር በሮችህም ሳንቃ ላይ ጻፋቸው። ይህን ብታደርግ እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ ሊሰጣቸው በመሐላ ቃል በገባላቸው ምድር የአንተና የልጆችህ ዘመን ከምድር በላይ እንዳለው ሰማይ ይረዝማል። “ስለዚህም እኔ የሰጠኋችሁን ትእዛዞች በጥንቃቄ ፈጽሙ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁን ውደዱ፤ በእርሱ መንገድም በመጓዝ ለእርሱ ታማኞች ሁኑ። ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር እነዚህን በፊታችሁ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ያስወጣል፤ እናንተም በብዛትና በኀይል ከእናንተ እጅግ ብርቱዎች የሆኑትን ሕዝቦች ምድር ትወርሳላችሁ። ስታልፉ በእግራችሁ የምትረግጡት መሬት ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም በደቡብ በኩል ካለው በረሓ ተነሥቶ በሰሜን በኩል እስካሉት እስከ ሊባኖስ ተራራዎች፥ እንዲሁም በምሥራቅ በኩል ከሚገኘው ከኤፍራጥስ ወንዝ ተነሥቶ በምዕራብ በኩል እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ሜዲቴራኒያን ባሕር ድረስ ይሰፋል። በዚያች ምድር በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ሕዝቦች ሁሉ እንዲፈሩአችሁ ያደርጋል፤ ሊቋቋማችሁ የሚችልም ከቶ አይገኝም።
ዘዳግም 11:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ተጠንቀቁ! ተታላችሁ ሌሎች አማልክትን እንዳታመልኩ፤ እንዳትሰግዱላቸውም። የጌታም ቁጣ በላያችሁ እንዳይነድ፤ እርሱም ዝናብ እንዳይከለክላችሁ፤ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም ጌታ ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ።” “እነዚህን ቃሎቼን፥ በልባችሁና በአእምሮአችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፥ በግምባራችሁም ላይ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ ቤት ስትቀመጥ፥ መንገድ ስትሄድ፥ ስትተኛና ስትነሣ ስለዚህ አጫውታቸው። በቤትህ መቃኖችና በግቢህ በሮች ላይ ጻፋቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ፥ ጌታ ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል።” “አምላካችሁን ጌታን ትወዱ ዘንድ፥ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፥ ከዚያም ጌታ እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፥ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ። በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፥ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው ባሕር ይደርሳል። ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ ጌታ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።”