ዘዳግም 1:19-28
ዘዳግም 1:19-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከኮሬብም ተጓዝን፤ አምላካችን እግዚአብሔርም እንዳዘዘን በታላቁ፥ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በአሞሬዎን ተራራ መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም አልኋችሁ፦ አምላካችን እግዚአብሔር እስከ ሰጣችሁ እስከ አሞሬዎን ተራራ ኑ፤ እነሆ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊታችሁ እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር እንዳላችሁ ውጡ፤ ውረሷት፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ አላችሁኝ። ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው ወሰድሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፤ ወደ ተራራውም ወጡ፤ ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆ መጥተው ሰለሉአት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፤ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፦ ‘አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት አሉን፤’ “ወደ እርስዋ መውጣትንም እንቢ አላችሁ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይም ዐመፃችሁ፤ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ፦ ‘እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞሬዎናውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ታላቅና ብዙ ነው፤ ከእኛም ይጠነክራሉ፤ ከተሞቹም ታላላቆች፥ የተመሸጉም፥ እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፤ የረዐይትንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት።’
ዘዳግም 1:19-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሰጥቷችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።” ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ። ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ። እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ። ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን። እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ። በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብጽ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው። ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረዣዥሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።”
ዘዳግም 1:19-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከኮሬብም ተጓዝን፥ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም፦ አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፤ እነሆ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊትህ አድርጎአል፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም አልኋችሁ። እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ምድሪቱን እንዲጎበኙልንና እንወጣበት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንስደድ አላችሁኝ። ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም አሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ጎበኙአት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፦ አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት ብለውም አወሩልን። በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርስዋ መውጣትን እንቢ አላችሁ፤ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ፦ እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን አጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት።
ዘዳግም 1:19-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ከዚያም እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን ከሲና ተነሥተን እናንተ ባያችሁት አስቸጋሪ በረሓ በተራራማው በአሞራውያን አገር በኩል አድርገን ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ሊያወርሰን የተሰፋ ቃል ወደገባልን ኮረብታማ ወደሆነችው ወደ አሞራውያን ምድር እነሆ፥ ደርሳችኋል፤ ተመልከቱ፤ አገሪቱ ይህችውላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ገብታችሁ ውረሱአት፤ በመፍራትም ተስፋ አትቊረጡ።’ “ነገር ግን እናንተ ወደ እኔ መጥታችሁ ‘ምድሪቱን የሚሰልሉ ሰዎችን በፊታችን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያች ምድር የሚያደርሰንን ትክክለኛ መንገድና ምን ዐይነት ከተሞችም እንዳሉ አጥንተው ሊነግሩን ይችላሉ’ አላችሁኝ። “ይህንንም ማድረግ መልካም መስሎ ስለ ታየኝ ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመምረጥ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላክሁ። እነርሱም ኮረብታማ ወደሆነችው አገር ዘልቀው በመግባት እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ተዘዋውረው አጠኑአት። በዚያም ካገኙት ፍሬ ጥቂቱን ይዘውልን መጡ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሊሰጠን ያቀዳት ምድር እጅግ ለም መሆንዋንም አስረዱን። “ነገር ግን እናንተ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፅ ወደዚያች ምድር መግባትን አልወደዳችሁም። እርስ በርሳችሁም እንዲህ ብላችሁ አጒረመረማችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ከግብጽ ምድርም ያወጣን እነዚህ አሞራውያን ይገድሉን ዘንድ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ፈልጎ ነው፤ ታዲያ እዚያ የምንሄደው ለምንድን ነው? እንፈራለን፤ የላክናቸውም ሰዎች በዚያ የሚኖሩት ሁሉ ብርቱዎችና በቁመታቸውም ከእኛ ይበልጥ ረጃጅሞች መሆናቸውን፥ እንዲሁም ርዝመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርስ የግንብ ቅጽሮች ባሉአቸው ከተሞች የሚኖሩ መሆናቸውን ነገሩን፤ እጅግ ግዙፋን የሆኑ የዔናቅ ልጆችንም አይተዋል።’
ዘዳግም 1:19-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ከኮሬብም ወጣን፥ ጌታ አምላካችን እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ሁሉ ባያችሁት ምድረ በዳ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፥ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም አልኋችሁ፦ ‘ጌታ አምላካችን ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፥ እነሆ፥ ጌታ አምላካችሁ ምድሪቱን በፊትህ አኑሮአል፥ የአባቶችህ አምላክ ጌታ እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፥ አትፍራ፥ አትደንግጥም።’ “እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ’ አላችሁኝ። “ነገሩ መልካም ሆኖ ታየኝ፥ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፥ ከየነገዱ ሁሉ አንዳንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ቃኙት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፥ አሉንም፦ ‘ጌታ አምላካችን የሚሰጠን ምድር መልካም ናት።’ “እናንተ ግን በጌታ በአምላካችሁ ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርሷ መውጣትን አልፈቀዳችሁም፥ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ ብላችሁ አጉረመረማችሁ፦ ‘ጌታ ስለ ጠላን በአሞራውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ፥ ሊያጠፋን ከግብጽ ምድር አወጣን። ወዴትስ እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው፥’ ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አወኩት።