የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 1

1
የእስራኤል ሕዝብ ከሲና ተነሥተው እንዲጓዙ የተሰጠ መመሪያ
1ከዮርዳኖስ ማዶ አራባ በሚባል ምድረ በዳ በሱፍ ፊት ለፊት በአንድ በኩል ፋራን፥ በሌላ በኩል ጦፌል፥ ላባን፥ ሐጼሮትና ዲዛሃብ መካከል ሳሉ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ንግግር ይህ ነው። 2ከሲና ተራራ ተነሥቶ በኤዶም ተራራ በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ ለመድረስ ዐሥራ አንድ ቀን ይፈጃል። #1፥2 ሲና፦ በሌሎች ቦታዎች ኮሬብ ተብሎ ይገኛል። #1፥2 ኤዶም ተራራ፦ ሲር ተራራ 3ግብጽን ለቀው ከወጡ በኋላ አርባኛው ዓመት በገባ በዐሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን ሙሴ ለሕዝቡ ያስረዳቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 4ይህም የሆነው በሐሴቦን ከተማ ነግሦ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንንና በዐስታሮትና በኤድረዒ ከተሞች ሆኖ ይገዛ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዖግን ድል ካደረገ በኋላ ነው። 5ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በሞአብ ምድር ሙሴ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤
6“በሲና ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲህ አለን፦ ‘እነሆ፦ በዚህ ተራራ ላይ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል፤ 7ሰፈራችሁን ነቅላችሁ ወደ ተራራማው የአሞራውያን አገር፥ ወደ ጐረቤትም ወደ አራባ በደጋውና በቈላው አገር፥ በኔጌብ፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ በኩል፥ በከነዓናውያን አገርና በሊባኖስ በኩል አድርጋችሁ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። 8እነሆ፥ ምድሪቱ በፊታችሁ ናት፤ እኔ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፥ እንዲሁም ለዘሮቻቸው ላወርሳቸው የተስፋ ቃል የገባሁላቸውን ምድር ሄዳችሁ ውረሱ።’ ”
ሙሴ የሕዝብ መሪዎችን መሾሙ
(ዘፀ. 18፥13-27)
9ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ገና በሲና ተራራ በነበርንበት ጊዜ እንዲህ ስል ነግሬአችሁ ነበር፤ ‘እናንተን የመምራት ኀላፊነት ለእኔ ይበዛብኛል፤ ይህን ሁሉ ብቻዬን ላደርግ አልችልም፤ 10እግዚአብሔር አምላካችሁ ቊጥራችሁን አብዝቶአል፤ እነሆ፥ አሁን ቊጥራችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዙ ነው፤ 11አሁንም የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ሺህ ጊዜ እጥፍ በመጨመር ቊጥራችሁን አብዝቶ ያበልጽጋችሁ! 12ነገር ግን በመካከላችሁ የሚነሣውን ጠብና ክርክር ለማስወገድ ይህን ከባድ ኀላፊነት ብቻዬን እንዴት ልሸከም እችላለሁ? 13ከእያንዳንዱ ነገድ የማስተዋል ጥበብ ያላቸውንና የሥራ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።’ 14እናንተም ‘ያቀረብከው ሐሳብ መልካም ነው’ ብላችሁ መልስ ሰጥታችሁኝ ነበር፤ 15ስለዚህም ከእያንዳንዱ ነገድ የመረጣችኋቸውን የሥራ ልምድ ያላቸውን ዐዋቂዎች መሪዎች ተቀብዬ ሾምኩላችሁ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ የሺህ አለቆች፥ አንዳንዶቹ የመቶ አለቆች፥ አንዳንዶቹም የኀምሳና የዐሥር አለቆች ሆነው የተሾሙ ነበሩ። ለነገዶችም ሁሉ ሌሎችንም ሹማምንት ሾምኩ።
16“በዚያን ጊዜ እነርሱን እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፤ ‘በሕዝባችሁ መካከል የሚነሣውን የጠብና የክርክር አቤቱታ አድምጡ፤ በራሳችሁ ሕዝብ ወይም በእናንተ ውስጥ በሚኖሩት መጻተኞች መካከል ስለሚነሣው ጠብና ክርክር ሁሉ በትክክል ፍረዱ። 17በምትሰጡትም ውሳኔ አድልዎ አታድርጉ፤ ስለ ማንኛውም ታላቅም ሆነ ታናሽ ሰው ያለ አድልዎ በእኩልነት ፍረዱ። ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ ማንንም አትፍሩ፤ ለእናንተ የሚከብድባችሁ ነገር ቢኖር ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም ውሳኔ እሰጥበታለሁ፤’ 18እናንተም ልታደርጉት ስለሚገባው ነገር ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ነገርኳችሁ።
ከቃዴስ በርኔ ሰላዮች ወደ ተስፋይቱ ምድር መላካቸው
(ዘኍ. 13፥1-33)
19“ከዚያም እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን ከሲና ተነሥተን እናንተ ባያችሁት አስቸጋሪ በረሓ በተራራማው በአሞራውያን አገር በኩል አድርገን ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። 20እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ሊያወርሰን የተሰፋ ቃል ወደገባልን ኮረብታማ ወደሆነችው ወደ አሞራውያን ምድር እነሆ፥ ደርሳችኋል፤ 21ተመልከቱ፤ አገሪቱ ይህችውላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ገብታችሁ ውረሱአት፤ በመፍራትም ተስፋ አትቊረጡ።’
22“ነገር ግን እናንተ ወደ እኔ መጥታችሁ ‘ምድሪቱን የሚሰልሉ ሰዎችን በፊታችን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያች ምድር የሚያደርሰንን ትክክለኛ መንገድና ምን ዐይነት ከተሞችም እንዳሉ አጥንተው ሊነግሩን ይችላሉ’ አላችሁኝ።
23“ይህንንም ማድረግ መልካም መስሎ ስለ ታየኝ ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመምረጥ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላክሁ። 24እነርሱም ኮረብታማ ወደሆነችው አገር ዘልቀው በመግባት እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ተዘዋውረው አጠኑአት። 25በዚያም ካገኙት ፍሬ ጥቂቱን ይዘውልን መጡ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሊሰጠን ያቀዳት ምድር እጅግ ለም መሆንዋንም አስረዱን።
26“ነገር ግን እናንተ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፅ ወደዚያች ምድር መግባትን አልወደዳችሁም። #ዘዳ. 9፥23፤ ዕብ. 3፥16። 27እርስ በርሳችሁም እንዲህ ብላችሁ አጒረመረማችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ከግብጽ ምድርም ያወጣን እነዚህ አሞራውያን ይገድሉን ዘንድ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ፈልጎ ነው፤ 28ታዲያ እዚያ የምንሄደው ለምንድን ነው? እንፈራለን፤ የላክናቸውም ሰዎች በዚያ የሚኖሩት ሁሉ ብርቱዎችና በቁመታቸውም ከእኛ ይበልጥ ረጃጅሞች መሆናቸውን፥ እንዲሁም ርዝመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርስ የግንብ ቅጽሮች ባሉአቸው ከተሞች የሚኖሩ መሆናቸውን ነገሩን፤ እጅግ ግዙፋን የሆኑ የዔናቅ ልጆችንም አይተዋል።’
29“ነገር ግን እኔ እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘ከእነዚህ ሕዝብ የተነሣ አትፍሩ፤ አትሸበሩም፤ 30በዓይናችሁ እያያችሁ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ለእናንተ የሚዋጋው በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው። 31እናንተ ወደዚህ ቦታ እስክትመጡ ድረስ አንድ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረ በዳው እንደ ተንከባከባችሁ አይታችኋል።’ #ሐ.ሥ. 13፥18። 32-33ይህም ሆኖ የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት ቀን በደመና ሌሊት በእሳት፥ በፊታችሁ በሚሄደው በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልተማመናችሁም። #ዕብ. 3፥19።
እግዚአብሔር እስራኤላውያንን መቅጣቱ
(ዘኍ. 14፥20-45)
34“እግዚአብሔርም የማጒረምረም ጩኸታችሁን ሰምቶ ተቈጣ፤ ስለዚህም እንዲህ ሲል ማለ፤ 35‘እኔ ለቀድሞ አባቶቻችሁ አወርሳታለሁ ብዬ የተስፋ ቃል ወደገባሁባት ወደዚያች ለም ምድር ከዚህ ክፉ ትውልድ መካከል አንዳችሁም አትገቡባትም። #ዕብ. 3፥18። 36ወደዚያች ምድር መግባት የሚችል የይፉኔ ልጅ ካሌብ ብቻ ነው፤ እርሱ በፍጹም ልቡ ታማኝ ሆኖ ስለ ተገኘ ያቺን የጐበኛትን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።’ 37በእናንተው ምክንያት እግዚአብሔር በእኔም ላይ እንኳ ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ ‘ሙሴ፥ አንተም ራስህ እንኳ ወደዚያች ምድር አትገባም፤ 38ነገር ግን የአንተ ረዳት የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ ወደ ምድሪቱ ይገባል፤ ምድሪቱን ይወርሱ ዘንድ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ አበረታታው።’
39“ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለሁላችንም እንዲህ አለ፤ ‘በጠላቶቻችን ይማረካሉ ያላችኋቸው ሕፃናትና ክፉና ደጉን ለይተው የማያውቁ ልጆቻችሁ ብቻ ወደዚያች ምድር ይገባሉ፤ ምድሪቱን ለእነርሱ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ይወርሱአታል። 40እናንተ ግን ወደ ቀይ ባሕር የሚወስደውን መንገድ በመከተል ወደ በረሓው ተመልሳችሁ ሂዱ።’
41“እናንተም ‘ሙሴ ሆይ፥ እኛ እግዚአብሔርን በድለናል፤ አሁን ግን አምላካችን እግዚአብሔር ባዘዘን መሠረት እንዋጋለን’ ብላችሁ መለሳችሁ፤ ኮረብታማይቱን አገር መውረር ቀላል መስሎአችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ለውጊያ ተዘጋጀ።
42“እግዚአብሔር ግን ‘እኔ ከእናንተ ጋር ስለማልሆን ለመዋጋት አትውጡ፤ ይህ ካልሆነ ጠላቶቻችሁ ድል ይመቱአችኋል’ በላቸው አለኝ። 43እግዚአብሔር ያለኝንም ለእናንተ ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን እምቢተኞች ሆናችሁ፤ በእርሱም ላይ ዐምፃችሁ በትዕቢታችሁ ብዛት ወደ ኮረብታማይቱ አገር ዘመታችሁ፤ 44በነዚያ ኮረብታዎች ላይ የሚኖሩ አሞራውያንም መጥተው ተጋጠሙአችሁ፤ ሠራዊታቸውም እንደ ንብ መንጋ ግር ብለው መጥተው እስከ ሆርማ ድረስ አሳደዱአችሁ፤ ኮረብታማ በሆነችው በኤዶም አገርም ድል አደረጉአችሁ። 45ስለዚህም ይረዳችሁ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን ጩኸታችሁን ሊያዳምጥና ሊረዳችሁ አልወደደም። 46ስለዚህም በቃዴስ ለረጅም ጊዜ ቈያችሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ