ዘዳግም 1:1-8
ዘዳግም 1:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በምዕራብ በኩል በኤርትራ ባሕር አጠገብ በፋራንና በጦፌል፥ በላባንና በአውሎን፥ በካታኪሪሲያም መካከል፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ፥ የነገራቸው ቃላት እኒህ ናቸው። በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን ጕዞ ነው። በአርባኛው ዓመት በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ እንዲነግራቸው እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው፤ በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞሬዎናውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስጣሮትና በኤድራይን ተቀምጦ የነበረውንም የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከገደሉት በኋላ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ “አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ በዚህ ተራራ መቀመጣችሁ በቃ፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ አሞራውያን ተራራ፥ ወደ አረባም ሀገሮች ሁሉ፥ በተራራውም፥ በሜዳውም፥ በሊባም፥ በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም ፊት ለፊት እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን ሰጠኋችሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ፥ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ምድር ውረሱ።
ዘዳግም 1:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ዓረባ በተባለው ምድረ በዳ ከሱጰ ትይዩ፣ በፋራንና በጦፌል፣ በላባን፣ በሐጼሮትና በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፣ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው። (በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን ያስሄዳል)። በአርባኛው ዓመት፣ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እስራኤላውያንን በሚመለከት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ሙሴ ለእነርሱ ነገራቸው። ይህ የሆነው በሐሴቦን ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንና በአስታሮት ይገዛ የነበረውን የዐግን ንጉሥ ባሳንን በኤድራይ ድል ካደረገ በኋላ ነው። ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሞዓብ ምድር ሳሉ፣ ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤ እግዚአብሔር አምላካችን (ያህዌ ኤሎሂም) በኮሬብ እንዲህ አለን፤ “እነሆ፤ በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል። ሰፈር ነቅላችሁ ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ጕዞ ቀጥሉ፤ ከዚያም በዓረባ፣ በተራሮቹ፣ በምዕራብ ኰረብታዎች ግርጌ፣ በኔጌብና በባሕሩ ዳርቻ ወዳሉት አጐራባች ሕዝቦች ሁሉ ሂዱ፤ እንዲሁም ወደ ከነዓናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ፣ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ዝለቁ። እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፣ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።”
ዘዳግም 1:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የአሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። በአርባኛው ዓመት በአሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ፥ በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህችን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ በዚህ ተራራ የተቀመጣችሁት በቃ፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር ወደ ድንበሮቹም ሁሉ፥ በዓረባም በደጋውም በቈላውም በደቡብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ።
ዘዳግም 1:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዮርዳኖስ ማዶ አራባ በሚባል ምድረ በዳ በሱፍ ፊት ለፊት በአንድ በኩል ፋራን፥ በሌላ በኩል ጦፌል፥ ላባን፥ ሐጼሮትና ዲዛሃብ መካከል ሳሉ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ንግግር ይህ ነው። ከሲና ተራራ ተነሥቶ በኤዶም ተራራ በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ ለመድረስ ዐሥራ አንድ ቀን ይፈጃል። ግብጽን ለቀው ከወጡ በኋላ አርባኛው ዓመት በገባ በዐሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን ሙሴ ለሕዝቡ ያስረዳቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። ይህም የሆነው በሐሴቦን ከተማ ነግሦ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንንና በዐስታሮትና በኤድረዒ ከተሞች ሆኖ ይገዛ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዖግን ድል ካደረገ በኋላ ነው። ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በሞአብ ምድር ሙሴ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤ “በሲና ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲህ አለን፦ ‘እነሆ፦ በዚህ ተራራ ላይ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል፤ ሰፈራችሁን ነቅላችሁ ወደ ተራራማው የአሞራውያን አገር፥ ወደ ጐረቤትም ወደ አራባ በደጋውና በቈላው አገር፥ በኔጌብ፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ በኩል፥ በከነዓናውያን አገርና በሊባኖስ በኩል አድርጋችሁ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱ በፊታችሁ ናት፤ እኔ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፥ እንዲሁም ለዘሮቻቸው ላወርሳቸው የተስፋ ቃል የገባሁላቸውን ምድር ሄዳችሁ ውረሱ።’ ”
ዘዳግም 1:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ትይዩ በሆነው ሱፍ ፊት ለፊት፥ በፋራን እና በጦፌልም፥ በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። ከኮሬብ በሴይር ተራራ መንገድ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። በአርባኛው ዓመት በዓሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን፥ ሙሴ፥ ጌታ ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ “ጌታ አምላካችን በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ ‘በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፥ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር፥ ወደ አጎራባቾቹም በዓረባም በደጋውና በቆላው ሁሉ፥ በኔጌብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አኖራለሁ፥ ግቡ፥ ጌታ ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ።’