ዘዳግም 1:1-33
ዘዳግም 1:1-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በምዕራብ በኩል በኤርትራ ባሕር አጠገብ በፋራንና በጦፌል፥ በላባንና በአውሎን፥ በካታኪሪሲያም መካከል፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ፥ የነገራቸው ቃላት እኒህ ናቸው። በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን ጕዞ ነው። በአርባኛው ዓመት በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ እንዲነግራቸው እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው፤ በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞሬዎናውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስጣሮትና በኤድራይን ተቀምጦ የነበረውንም የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከገደሉት በኋላ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ “አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ በዚህ ተራራ መቀመጣችሁ በቃ፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ አሞራውያን ተራራ፥ ወደ አረባም ሀገሮች ሁሉ፥ በተራራውም፥ በሜዳውም፥ በሊባም፥ በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም ፊት ለፊት እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን ሰጠኋችሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ፥ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ምድር ውረሱ። “በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ፦ እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር አብዝቶአችኋልና፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዙዎች ናችሁ። የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ቍጥር ላይ እልፍ አእላፋት ይጨምር፤ እንደ ተናገራችሁም ይባርካችሁ። እኔ ብቻዬን ድካማችሁን፥ ሸክማችሁንም፥ ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች፥ አስተዋዮችም፥ ዐዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች አምጡ፤ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ። እናንተም፦ ‘እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው’ ብላችሁ መልሳችሁ ነገራችሁኝ። ከእናንተም ጥበበኞችና ዐዋቂዎች፥ አስተዋዮችም የሆኑትን ሰዎች ወሰድሁ፤ በእናንተም ላይ አለቆች፥ የሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ የአምሳ አለቆችም፥ የዐሥር አለቆችም፥ ለፈራጆቻችሁም ጻፎች አድርጌ ሰየምኋቸው። በዚያን ጊዜ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። አልኋቸውም፦ የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፤ በሰውና በወንድሙ፥ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። በፍርድም ፊት አትዩ፤ ለትልቁም፥ ለትንሹም በእውነት ፍረዱ፤ ለሰው ፊት አታድሉ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ነውና። አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም እሰማዋለሁ፤ በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ። “ከኮሬብም ተጓዝን፤ አምላካችን እግዚአብሔርም እንዳዘዘን በታላቁ፥ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በአሞሬዎን ተራራ መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም አልኋችሁ፦ አምላካችን እግዚአብሔር እስከ ሰጣችሁ እስከ አሞሬዎን ተራራ ኑ፤ እነሆ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊታችሁ እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር እንዳላችሁ ውጡ፤ ውረሷት፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ አላችሁኝ። ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው ወሰድሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፤ ወደ ተራራውም ወጡ፤ ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆ መጥተው ሰለሉአት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፤ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፦ ‘አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት አሉን፤’ “ወደ እርስዋ መውጣትንም እንቢ አላችሁ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይም ዐመፃችሁ፤ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ፦ ‘እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞሬዎናውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ታላቅና ብዙ ነው፤ ከእኛም ይጠነክራሉ፤ ከተሞቹም ታላላቆች፥ የተመሸጉም፥ እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፤ የረዐይትንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት።’ እኔም አልኋችሁ፦ አትደንግጡ፤ ከእነርሱም አትፍሩ፤ በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ በግብፅ ምድር እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ አብሮአችሁ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲመግብ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረ በዳ እንደመገባችሁ እናንተ አይታችኋል። ዳሩ ግን በዚህ ነገር አምላካችሁ እግዚአብሔርን አላመናችሁትም። እርሱም ስፍራን እንዲመርጥላችሁ፥ ትሄዱበትም ዘንድ የሚገባውን መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አላመናችሁትም።
ዘዳግም 1:1-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ዓረባ በተባለው ምድረ በዳ ከሱጰ ትይዩ፣ በፋራንና በጦፌል፣ በላባን፣ በሐጼሮትና በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፣ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው። (በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን ያስሄዳል)። በአርባኛው ዓመት፣ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እስራኤላውያንን በሚመለከት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ሙሴ ለእነርሱ ነገራቸው። ይህ የሆነው በሐሴቦን ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንና በአስታሮት ይገዛ የነበረውን የዐግን ንጉሥ ባሳንን በኤድራይ ድል ካደረገ በኋላ ነው። ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሞዓብ ምድር ሳሉ፣ ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤ እግዚአብሔር አምላካችን (ያህዌ ኤሎሂም) በኮሬብ እንዲህ አለን፤ “እነሆ፤ በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል። ሰፈር ነቅላችሁ ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ጕዞ ቀጥሉ፤ ከዚያም በዓረባ፣ በተራሮቹ፣ በምዕራብ ኰረብታዎች ግርጌ፣ በኔጌብና በባሕሩ ዳርቻ ወዳሉት አጐራባች ሕዝቦች ሁሉ ሂዱ፤ እንዲሁም ወደ ከነዓናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ፣ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ዝለቁ። እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፣ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።” እኔም በዚያን ጊዜ እንዲህ አልኋችሁ፤ “ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቍጥራችሁን ጨምሯል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል። አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሺሕ ጊዜ ያብዛችሁ፣ በሰጠውም ተስፋ መሠረት ይባርካችሁ! ይሁን እንጂ ችግራችሁን፣ ሸክማችሁንና ክርክራችሁን ሁሉ ብቻዬን እንዴት አድርጌ መሸከም እችላለሁ? ጥበበኞችን፣ አስተዋዮችንና የተከበሩ ሰዎችን ከየነገዳችሁ ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።” እናንተም፣ “ይደረግ ዘንድ ያቀረብኸው ሐሳብ መልካም ነው” ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች ጥበበኞችንና የተከበሩትን ሰዎች ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ አምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው። በዚያን ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በትክክል ፍረዱ። በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።” በዚያን ጊዜ ማድረግ የነበረባችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ። ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምድሪቱን ሰጥቷችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።” ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ። ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ። እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ። ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን። እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ። በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብፅ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው። ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረጃጅሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።” እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም። በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤ በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።” ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አልታመናችሁም፤ በጕዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር።
ዘዳግም 1:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የአሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። በአርባኛው ዓመት በአሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ፥ በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህችን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ በዚህ ተራራ የተቀመጣችሁት በቃ፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር ወደ ድንበሮቹም ሁሉ፥ በዓረባም በደጋውም በቈላውም በደቡብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ። በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ፦ እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር አብዝቶአችኋል፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ። የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ቍጥር ላይ እልፍ አእላፋት ይጨምር፥ እንደ ተናገራችሁም ይባርካችሁ። እኔ ብቻዬን ድካምችሁን ሸክማችሁንም ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ። እናንተም፦ እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች መረጥሁ፥ በእናንተም ላይ አለቆች የሻለቆችም የመቶ አለቆችም የአምሳ አለቆችም የአሥር አለቆችም ገዦችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው። በዚያን ጊዜም፦ የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፤ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፤ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፤ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፤ ከነገርም አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም እሰማዋለሁ ብዬ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ። ከኮሬብም ተጓዝን፥ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም፦ አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፤ እነሆ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊትህ አድርጎአል፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም አልኋችሁ። እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ምድሪቱን እንዲጎበኙልንና እንወጣበት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንስደድ አላችሁኝ። ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም አሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ጎበኙአት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፦ አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት ብለውም አወሩልን። በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርስዋ መውጣትን እንቢ አላችሁ፤ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ፦ እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን አጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት። እኔም አልኋችሁ፦ አትደንግጡ፥ ከእነርሱም አትፍሩ፤ በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እናንተ ስታዩ በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲሸከም አምላክህ እግዚአብሔር እንደተሸከመህ አንተ አይተሃል። ዳሩ ግን ለሰፈራችሁ የሚገባውን ስፍራ እንዲፈልግላችሁ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን በዚህ ነገር አላመናችሁም።
ዘዳግም 1:1-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዮርዳኖስ ማዶ አራባ በሚባል ምድረ በዳ በሱፍ ፊት ለፊት በአንድ በኩል ፋራን፥ በሌላ በኩል ጦፌል፥ ላባን፥ ሐጼሮትና ዲዛሃብ መካከል ሳሉ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ንግግር ይህ ነው። ከሲና ተራራ ተነሥቶ በኤዶም ተራራ በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ ለመድረስ ዐሥራ አንድ ቀን ይፈጃል። ግብጽን ለቀው ከወጡ በኋላ አርባኛው ዓመት በገባ በዐሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን ሙሴ ለሕዝቡ ያስረዳቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። ይህም የሆነው በሐሴቦን ከተማ ነግሦ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንንና በዐስታሮትና በኤድረዒ ከተሞች ሆኖ ይገዛ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዖግን ድል ካደረገ በኋላ ነው። ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ በሞአብ ምድር ሙሴ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤ “በሲና ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን እንዲህ አለን፦ ‘እነሆ፦ በዚህ ተራራ ላይ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል፤ ሰፈራችሁን ነቅላችሁ ወደ ተራራማው የአሞራውያን አገር፥ ወደ ጐረቤትም ወደ አራባ በደጋውና በቈላው አገር፥ በኔጌብ፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ በኩል፥ በከነዓናውያን አገርና በሊባኖስ በኩል አድርጋችሁ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱ በፊታችሁ ናት፤ እኔ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፥ እንዲሁም ለዘሮቻቸው ላወርሳቸው የተስፋ ቃል የገባሁላቸውን ምድር ሄዳችሁ ውረሱ።’ ” ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ገና በሲና ተራራ በነበርንበት ጊዜ እንዲህ ስል ነግሬአችሁ ነበር፤ ‘እናንተን የመምራት ኀላፊነት ለእኔ ይበዛብኛል፤ ይህን ሁሉ ብቻዬን ላደርግ አልችልም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቊጥራችሁን አብዝቶአል፤ እነሆ፥ አሁን ቊጥራችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዙ ነው፤ አሁንም የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ሺህ ጊዜ እጥፍ በመጨመር ቊጥራችሁን አብዝቶ ያበልጽጋችሁ! ነገር ግን በመካከላችሁ የሚነሣውን ጠብና ክርክር ለማስወገድ ይህን ከባድ ኀላፊነት ብቻዬን እንዴት ልሸከም እችላለሁ? ከእያንዳንዱ ነገድ የማስተዋል ጥበብ ያላቸውንና የሥራ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።’ እናንተም ‘ያቀረብከው ሐሳብ መልካም ነው’ ብላችሁ መልስ ሰጥታችሁኝ ነበር፤ ስለዚህም ከእያንዳንዱ ነገድ የመረጣችኋቸውን የሥራ ልምድ ያላቸውን ዐዋቂዎች መሪዎች ተቀብዬ ሾምኩላችሁ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ የሺህ አለቆች፥ አንዳንዶቹ የመቶ አለቆች፥ አንዳንዶቹም የኀምሳና የዐሥር አለቆች ሆነው የተሾሙ ነበሩ። ለነገዶችም ሁሉ ሌሎችንም ሹማምንት ሾምኩ። “በዚያን ጊዜ እነርሱን እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፤ ‘በሕዝባችሁ መካከል የሚነሣውን የጠብና የክርክር አቤቱታ አድምጡ፤ በራሳችሁ ሕዝብ ወይም በእናንተ ውስጥ በሚኖሩት መጻተኞች መካከል ስለሚነሣው ጠብና ክርክር ሁሉ በትክክል ፍረዱ። በምትሰጡትም ውሳኔ አድልዎ አታድርጉ፤ ስለ ማንኛውም ታላቅም ሆነ ታናሽ ሰው ያለ አድልዎ በእኩልነት ፍረዱ። ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ ማንንም አትፍሩ፤ ለእናንተ የሚከብድባችሁ ነገር ቢኖር ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም ውሳኔ እሰጥበታለሁ፤’ እናንተም ልታደርጉት ስለሚገባው ነገር ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ነገርኳችሁ። “ከዚያም እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን ከሲና ተነሥተን እናንተ ባያችሁት አስቸጋሪ በረሓ በተራራማው በአሞራውያን አገር በኩል አድርገን ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ሊያወርሰን የተሰፋ ቃል ወደገባልን ኮረብታማ ወደሆነችው ወደ አሞራውያን ምድር እነሆ፥ ደርሳችኋል፤ ተመልከቱ፤ አገሪቱ ይህችውላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ገብታችሁ ውረሱአት፤ በመፍራትም ተስፋ አትቊረጡ።’ “ነገር ግን እናንተ ወደ እኔ መጥታችሁ ‘ምድሪቱን የሚሰልሉ ሰዎችን በፊታችን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያች ምድር የሚያደርሰንን ትክክለኛ መንገድና ምን ዐይነት ከተሞችም እንዳሉ አጥንተው ሊነግሩን ይችላሉ’ አላችሁኝ። “ይህንንም ማድረግ መልካም መስሎ ስለ ታየኝ ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመምረጥ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላክሁ። እነርሱም ኮረብታማ ወደሆነችው አገር ዘልቀው በመግባት እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ተዘዋውረው አጠኑአት። በዚያም ካገኙት ፍሬ ጥቂቱን ይዘውልን መጡ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሊሰጠን ያቀዳት ምድር እጅግ ለም መሆንዋንም አስረዱን። “ነገር ግን እናንተ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ በማመፅ ወደዚያች ምድር መግባትን አልወደዳችሁም። እርስ በርሳችሁም እንዲህ ብላችሁ አጒረመረማችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ጠልቶናል፤ ከግብጽ ምድርም ያወጣን እነዚህ አሞራውያን ይገድሉን ዘንድ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ፈልጎ ነው፤ ታዲያ እዚያ የምንሄደው ለምንድን ነው? እንፈራለን፤ የላክናቸውም ሰዎች በዚያ የሚኖሩት ሁሉ ብርቱዎችና በቁመታቸውም ከእኛ ይበልጥ ረጃጅሞች መሆናቸውን፥ እንዲሁም ርዝመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርስ የግንብ ቅጽሮች ባሉአቸው ከተሞች የሚኖሩ መሆናቸውን ነገሩን፤ እጅግ ግዙፋን የሆኑ የዔናቅ ልጆችንም አይተዋል።’ “ነገር ግን እኔ እንዲህ ብዬ ነገርኳችሁ፤ ‘ከእነዚህ ሕዝብ የተነሣ አትፍሩ፤ አትሸበሩም፤ በዓይናችሁ እያያችሁ በግብጽ እንዳደረገላችሁ ለእናንተ የሚዋጋው በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው። እናንተ ወደዚህ ቦታ እስክትመጡ ድረስ አንድ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረ በዳው እንደ ተንከባከባችሁ አይታችኋል።’ ይህም ሆኖ የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት ቀን በደመና ሌሊት በእሳት፥ በፊታችሁ በሚሄደው በአምላካችሁ በእግዚአብሔር አልተማመናችሁም።
ዘዳግም 1:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ትይዩ በሆነው ሱፍ ፊት ለፊት፥ በፋራን እና በጦፌልም፥ በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። ከኮሬብ በሴይር ተራራ መንገድ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። በአርባኛው ዓመት በዓሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን፥ ሙሴ፥ ጌታ ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦ “ጌታ አምላካችን በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ ‘በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፥ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር፥ ወደ አጎራባቾቹም በዓረባም በደጋውና በቆላው ሁሉ፥ በኔጌብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አኖራለሁ፥ ግቡ፥ ጌታ ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ።’ “በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ፦ ‘እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፥ ጌታ አምላካችሁ አብዝቶአችኋል፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ። የአባቶቻችሁ አምላክ፥ ጌታ እንደ ተናገራችሁም፥ በዚህ ቍጥር ላይ ሺህ ጊዜ እጥፍ ይጨምር፥ ይባርካችሁም። እኔ ብቻዬን ድካምችሁን፥ ሸክማችሁንም፥ ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች፥ አስተዋዮች፥ አዋቂዎች የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ።’ እናንተም፦ ‘እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው፥’ ብላችሁ መለሳችሁልኝ። እኔም ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች ተቀበልኩ፥ በእናንተም ላይ የሺህ አለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ የኀምሳ አለቆችም፥ የዐሥር አለቆችም ገዢዎችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው። በዚያን ጊዜ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። አልኋቸውም፦ ‘የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፥ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፥ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፥ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፥ አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም እሰማዋለሁ፤’ በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ። “ከኮሬብም ወጣን፥ ጌታ አምላካችን እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ሁሉ ባያችሁት ምድረ በዳ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፥ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። እኔም አልኋችሁ፦ ‘ጌታ አምላካችን ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፥ እነሆ፥ ጌታ አምላካችሁ ምድሪቱን በፊትህ አኑሮአል፥ የአባቶችህ አምላክ ጌታ እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፥ አትፍራ፥ አትደንግጥም።’ “እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ’ አላችሁኝ። “ነገሩ መልካም ሆኖ ታየኝ፥ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፥ ከየነገዱ ሁሉ አንዳንድ ሰው ነበረ። ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ቃኙት። ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፥ አሉንም፦ ‘ጌታ አምላካችን የሚሰጠን ምድር መልካም ናት።’ “እናንተ ግን በጌታ በአምላካችሁ ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርሷ መውጣትን አልፈቀዳችሁም፥ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ ብላችሁ አጉረመረማችሁ፦ ‘ጌታ ስለ ጠላን በአሞራውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ፥ ሊያጠፋን ከግብጽ ምድር አወጣን። ወዴትስ እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው፥’ ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አወኩት። “እኔም አልኋችሁ፦ ‘አትሸበሩ፥ እነርሱንም አትፍሩ፥ በዓይናችሁ ፊት በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ በፊታችሁ የሚሄደው ጌታ አምላካችሁ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ በምድረ በዳም፥ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ፥ ጌታ አምላካችሁ እንዴት እንደተንከባከባችሁ አይታችኋል።’ ይህም ሆኖ በዚህ ነገር ጌታ አምላካችሁን አላመናችሁም፤ እርሱ ግን የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ ለማሳየት ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን ጌታ አምላካችሁን አላመናችሁም።