ቈላስይስ 4:2-18
ቈላስይስ 4:2-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በምስጋና እየተጋችሁ ለጸሎት ፅሙዳን ሁኑ። ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድንናገር፥ እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፤ ለምኑልንም፤ ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ። ዘመኑን እየዋጃችሁ ከሃይማኖት ወደ ተለዩ ሰዎች በማስተዋል ሂዱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምትመልሱ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደ ተቀመመ በጸጋ ይሁን። የተወደደ ወንድማችንና የታመነ አገልጋይ፥ በጌታ ሥራም ተባባሪያችን የሆነ ቲኪቆስ የእኔን ዜና ይነግራችኋል። ስለዚህ ሥራ ወደ እናንተ የላክሁት ዜናዬን ታውቁ ዘንድ፥ ልባችሁንም ያጽናና ዘንድ ነው። ወገናችሁ ከሆነው ከምንወደውና ከታመነው ወንድማችን ከአናሲሞስ ጋር፥ እነርሱ ሥራችንንና ያለንበትን ያስረዱአችኋል። ከእኔ ጋር የተማረከው አርስጥሮኮስ፥ ወደ እናንተ በሚመጣ ጊዜ ትቀበሉት ዘንድ ስለ እርሱ ያዘዝኋችሁ የበርናባስ የአባቱ ወንድም ልጅ ማርቆስም፥ ኢዮስጦስ የተባለ ኢያሱም፥ ከግዙራን ሰዎች ወገን የሚሆኑ እነዚህ ሰላም ይሏችኋል። በእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ረዳቶች እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም እኔን አጽናንተውኛል። ከእናንተ ወገን የሚሆን ኤጳፍራስም ሰላም ይላችኋል፥ እርሱ የክርስቶስ አገልጋይ ነው፤ እግዚአብሔር በሚወደው ነገር ሁሉ ምሉኣንና ፍጹማን እንድትሆኑ፥ ስለ እናንተ ዘወትር ይጸልያል፤ ይማልዳልም። እጅግ እንደሚወዳችሁና ስለ እናንተ በሎዶቅያና በኢያራ ከተማ ስላሉትም እንደሚቈረቈር እኔ ምስክሩ ነኝ። ወዳጃችን ባለ መድኃኒቱ ሉቃስም ሰላም ብሎአችኋል፤ ዴማስም ሰላም ይላችኋል። በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞቻችንና ለንምፋን፥ በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ይህችን መልእክት እናንተ አንብባችሁ፥ በቤተ ክርስቲያን ያነብቡአት ዘንድ ወደ ሎዶቅያ ላኩአት፤ ዳግመኛም እናንተ ከሎዶቅያ የጻፍኋትን መልእክት አንብቡአት። አክርጳንም “ከእግዚአብሔር የተሾምህባትን መልእክትህን እንድትፈጽማት ተጠንቀቅ” በሉት። እኔ ጳውሎስ በእጄ ጽፌ ሰላም አልኋችሁ፤ እስራቴን አስቡ፤ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲኪቆስ እጅ ወደ ቈላስይስ ሰዎች የተላከችው መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።
ቈላስይስ 4:2-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከማመስገን ጋራ ነቅታችሁ በትጋት ጸልዩ። እኔ እስረኛ የሆንሁለትን የክርስቶስን ምስጢር ማወጅ እንድንችል፣ እግዚአብሔር የቃሉን በር እንዲከፍትልን ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤ ደግሞም መናገር እንደሚገባኝ ቃሉን በግልጽ እንድናገር ጸልዩልኝ። በውጭ ካሉት ሰዎች ጋራ ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ ተመላለሱ፤ በተገኘውም ዕድል ሁሉ ተጠቀሙ። ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን። ቲኪቆስ ስላለሁበት ሁኔታ በሙሉ ይነግራችኋል፤ እርሱ የተወደደ ወንድምና ታማኝ አገልጋይ፣ በጌታም ዐብሮኝ ባሪያ ነው። ስላለንበት ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ለዚህ ጕዳይ ወደ እናንተ እልከዋለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ወገን ከሆነው ከታማኙና ከተወዳጁ ወንድማችን ከአናሲሞስ ጋራ ወደ እናንተ ይመጣል፤ እነርሱም እዚህ ስላለው ሁኔታ ሁሉ ይነግሯችኋል። ዐብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስና የበርናባስ የአክስቱ ልጅ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ስለ ማርቆስ መመሪያ ደርሷችኋል፤ እንግዲህ ወደ እናንተ ሲመጣ ተቀበሉት። ኢዮስጦስ የተባለው ኢያሱም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ከተገረዙት መካከል ለእግዚአብሔር መንግሥት ዐብረውኝ የሚሠሩት፣ እኔንም ያጽናኑኝ እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም አጽናንተውናል። ከእናንተ ወገን የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እርሱም ፍጹም ጠንክራችሁና ሙሉ በሙሉ ተረጋግታችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ዘወትር ስለ እናንተ በጸሎት እየተጋደለ ነው። ደግሞም ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በኢያራ ከተሞች ስላሉት ተግቶ እንደሚሠራ እኔ እመሰክርለታለሁ። የተወደደው ሐኪሙ ሉቃስ እንዲሁም ዴማስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞች፣ ለንምፉን፣ በቤቷም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ይህች መልእክት ከተነበበችላችሁ በኋላ በሎዶቅያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ እናንተም ደግሞ በሎዶቅያ ያለችውን መልእክት አንብቡ። ለአርክጳም፣ “በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት ከፍጻሜ ለማድረስ ተጠንቀቅ” በሉልኝ። ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍሁት እኔ ጳውሎስ ነኝ። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን።
ቈላስይስ 4:2-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤ ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ። ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ ቲኪቆስ ኑሮዬን ሁሉ ያስታውቃችኋል፤ ወሬያችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና፥ ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከአናሲሞስ ጋር ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው፤ የዚህን ስፍራ ወሬ ሁሉ ያስታውቁአችኋል። ከተገረዙት ወገን ያሉት፥ አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ስለ ማርቆስ፦ ወደ እናንተ ቢመጣ፥ ተቀበሉት የሚል ትእዛዝ ተቀበላችሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፥ እኔንም አጽናንተውኛል። ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል። ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና። የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን። ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ። ለአክሪጳም፦ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ። በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
ቈላስይስ 4:2-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርን ተግታችሁ በማመስገን ባለማቋረጥ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር እግዚአብሔር ለቃሉ በር እንዲከፍትልንና እኔ በእርሱ ምክንያት ታስሬ የምገኝበትን የክርስቶስን ምሥጢር ማብሠር እንድንችል ለእኛም ጸልዩ። እኔም እንደሚገባኝ ቃሉን በግልጥ እንድናገር ጸልዩልኝ። በማንኛውም አጋጣሚ ጊዜ እየተጠቀማችሁ በማያምኑት ሰዎች ዘንድ በጥበብ ኑሩ። ለእያንዳንዱ ሰው ተገቢውን መልስ መስጠት እንድታውቁ ዘወትር ንግግራችሁ ለዛና ጣዕም ያለው ይሁን። ቲኪቆስ ስለ እኔ ጉዳይ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል፤ እርሱ ተወዳጅ ወንድም፥ ታማኝ አገልጋይና በጌታ ሥራም የአገልግሎት ጓደኛዬ ነው። እርሱን ወደ እናንተ የላክሁበት ምክንያት ስለ እኛ ሁኔታ እንዲነግራችሁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ነው። ከእርሱም ጋር የእናንተ ወገን የሆነው የታመነውና የተወደደው ወንድም ኦኔሲሞስ ወደ እናንተ ይመጣል፤ እነርሱ በዚህ ስፍራ ስላለው ነገር ሁሉ ያስታውቋችኋል። ከእኔ ጋር የታሰረው አርስጥሮኮስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ አንድ ጊዜ፥ “ወደ እናንተ በሚመጣበት ጊዜ እንድትቀበሉት” ብዬ አሳስቤአችሁ የነበረው የበርናባስ የአጐቱ ልጅ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ኢዮስጦስ ተብሎም የሚጠራው ኢያሱ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው ከሚሠሩት ሰዎች መካከል የአይሁድ ወገኖች የሆኑት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እኔንም አጽናንተውኛል። የእናንተ ወገን የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ኤጳፍራም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በመንፈሳዊ ሕይወት በማደግ ጸንታችሁ እንድትቆሙና የእግዚአብሔርንም ፈቃድ በሙሉ እንድትፈጽሙ እርሱ ስለ እናንተ በጸሎቱ ዘወትር ይጸልያል። ስለ እናንተ በሎዶቅያና በሂራፖሊስ ከተሞች ስላሉትም ሰዎች በጣም እንደሚደክም እኔ ራሴ እመሰክርለታለሁ። የተወደደው ሐኪም ሉቃስና ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞች ለንምፉና በቤትዋም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ይህችን መልእክት እናንተ ካነበባችኋት በኋላ በሎዶቅያ ሰዎች ዘንድ ባለችው ቤተ ክርስቲያን እንድትነበብ አድርጉ፤ እናንተም ከሎዶቅያ የሚላክላችሁን መልእክት አንብቡ። ለአርኪጳስም “በጌታ አገልግሎት የተሰጠህን ሥራ በጥንቃቄ እንድትፈጽም” ብላችሁ ንገሩልኝ። ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍኩት እኔ ጳውሎስ ነኝ፤ በሰንሰለት ታስሬ እንዳለሁ አስታውሱ። የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
ቈላስይስ 4:2-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከማመስገን ጋር በጸሎት ውስጥ ነቅታችሁ ያለማቋረጥ ትጉ፤ የታሰርኩበት ምክንያት የሆነውን የክርስቶስን ምሥጢር ለማወጅ እግዚአብሔር ለቃሉ በር እንዲከፍትልን ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤ ቃሉንም መናገር እንደሚገባኝ ያህል ለመግለጥ እንድችል ጸልዩልኝ። ዘመኑን እየዋጃችሁ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ እንድታውቁ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባርያ የሆነ ቲኪቆስ እኔ ስላለሁበት ሁኔታ ሁሉ ይነግራችኋል፤ እርሱን ወደ እናንተ የላክሁበት ዋነኛ ዓላማ እኛ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምንገኝ እንዲያሳውቃችሁና ልባችሁንም እንዲያጽናና ነው፤ ቲቂቆስም ከእናንተ ወገን ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከኦኔሲሞስ ጋር አብሮ ይመጣል። በእዚህም ሥፍራ ስላለው ሁኔታ ሁሉ ያስታውቋችኋል። “ወደ እናንተ ቢመጣ፥ ተቀበሉት፤” የሚል ትእዛዝ የተቀበላችሁለት የበርናባስ የወንድሙ ልጅ ማርቆስ እንዳረገው እንዲሁ አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ከተገረዙትም ወገን የሆኑ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እኔንም አጽናንተውኛል። ከእናንተ ወገን የሆነ የክርስቶስ ባርያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይተጋል። ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ በሥራ እንደደከመ እመሰክርለታለሁና። የተወደደው ሐኪም ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤትዋም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ይህም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበ በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንዲነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምታገኙትን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ። ለአክሪጳም፦ “በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ!” በሉልኝ። ይህን ሰላምታ እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ ጽፌዋለሁ። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።