ቈላስይስ 1:19-22
ቈላስይስ 1:19-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሁሉ በእርሱ ፍጹም ሆኖ ይኖር ዘንድ፥ ወዶአልና። ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አደረገ። እናንተም ቀድሞ በአሳባችሁና በክፉ ሥራችሁ ከእግዚአብሔር የተለያችሁና ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።
ቈላስይስ 1:19-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወድዷልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ። ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በዐሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፣ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤
ቈላስይስ 1:19-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ።
ቈላስይስ 1:19-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህም የሆነው የመለኮት ሙላት በልጁ እንዲኖር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ስለ ሆነ ነው። በእርሱም አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በልጁ ደምም ሰላምን አደረገ። ቀድሞ ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ትኖሩ ነበር፤ በሐሳባችሁና በክፉ ሥራችሁም ምክንያት ጠላቶቹ ነበራችሁ። አሁን ግን ቅዱሳንና ንጹሓን፥ ነቀፋም የሌለባችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ፥ ልጁ በሥጋ በመሞቱ ምክንያት እግዚአብሔር ከራሱ ጋር አስታረቃችሁ።