ቈላስይስ 1:16-18
ቈላስይስ 1:16-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእርሱ ቃልነት እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአልና በሰማይ ያለውን፥ በምድርም ያለውን፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ መናብርትም ቢሆኑ፥ አጋእዝትም ቢሆኑ፥ መኳንንትም ቢሆኑ፥ ቀደምትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእርሱ ቃልነት ፈጥሮአቸዋልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ፤ እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእርሱ ጸና። እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በኵር እርሱ ለሁሉ ራስ ይሆን ዘንድ ከሙታን ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአልና።
ቈላስይስ 1:16-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው።
ቈላስይስ 1:15-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።
ቈላስይስ 1:16-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር ቀዳሚ እንዲሆን፤ ከሞት በመነሣትም ፊተኛና መጀመሪያ ነው።