ቈላስይስ 1:10-14
ቈላስይስ 1:10-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ እግዚአብሔር በሚገባችሁ ትሄዱ ዘንድ፥ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፥ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ፥ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ። በፍጹም ኀይል፥ በክብሩ ጽናት፥ በፍጹም ትዕግሥት፥ በተስፋና በደስታም ጸንታችሁ። በብርሃን ቅዱሳን ለሚታደሉት ርስት የበቃን ያደረገንን እግዚአብሔር አብን አመስግኑት። ከጨለማ አገዛዝ አዳነን፤ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥትም መለሰን። ድኅነትን ያገኘንበት፥ ኀጢአታችንም የተሠረየበት ነው።
ቈላስይስ 1:10-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣ በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው። እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።
ቈላስይስ 1:10-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።
ቈላስይስ 1:10-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት። እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል።
ቈላስይስ 1:10-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህም በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና በእግዚአብሔር እውቀት እያደጋችሁ፥ ለጌታ እንደሚገባው ፍጹም ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድትኖሩ ነው። እንደ ክብሩ ኃያልነት በሁሉ ኃይል እንድትበረቱና ሁሉንም ነገር በትዕግሥት በጽኑ ለመወጣት እንድትዘጋጁ እንዲሁም ደስ በመሰኘት በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን።