አሞጽ 1:2-10
አሞጽ 1:2-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም አለ፥ “እግዚአብሔር ከጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ ከኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ የእረኞችም ማሰማሪያዎች ያለቅሳሉ፤ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የገለዓድን ነፍሰ ጡሮች በብረት መጋዝ ሰንጥቀዋቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። በአዛሄል ቤት ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የወልደ አዴርንም መሠረቶች ትበላለች። የደማስቆንም ቍልፎች እሰብራለሁ፤ በአዎን ሸለቆ የሚኖሩትንም ሰዎች አጠፋለሁ፤ የካራን ሰዎች ወገኖችንም እቈራርጣለሁ፤ የሶርያ ሕዝብም ወደ ቂር ይማረካሉ፤” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በኤዶምያስ ይዘጉባቸው ዘንድ የሰሎሞንን ምርኮ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ መሠረቶችዋንም ትበላለች። የአዛጦን ነዋሪዎችን አጠፋለሁ፤ የአስቀሎናም ሕዝብ ይጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፤ ከፍልስጥኤማውያን የቀሩትም ይጠፋሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የሰሎሞን ምርኮኞችን በኤዶምያስ ዘግተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኀጢአት አልመለስላቸውም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን አሰድዳለሁ፤ መሠረቶችዋንም ትበላለች።”
አሞጽ 1:2-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ከጽዮን ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማል፤ ከኢየሩሳሌምም ያንጐደጕዳል፤ የእረኞች ማሰማሪያዎች ደርቀዋል፤ የቀርሜሎስም ዐናት ጠውልጓል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የደማስቆ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ የብረት ጥርስ ባለው ማሄጃ፣ ገለዓድን አሂዳለችና፤ የወልደ አዴርን ምሽጎች እንዲበላ፣ በአዛሄል ቤት ላይ እሳት እሰድዳለሁ። የደማስቆን በሮች እሰባብራለሁ፤ በቤት ዔደን በትር የያዘውን፣ በአዌን ሸለቆ ያለውን ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርኮ ወደ ቂር ይሄዳል” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የጋዛ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ሕዝቡን ሁሉ ማርካ በመውሰድ፣ ለኤዶም ሸጣለችና። ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በጋዛ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ። በአስቀሎና በትር የያዘውን፣ የአሽዶድንም ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ በፍልስጥኤም ካሉት የመጨረሻው ሰው እስኪሞት ድረስ፣ እጄን በአቃሮን ላይ እዘረጋለሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የጢሮስ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም። የወንድማማችነትን ቃል ኪዳን በማፍረስ፣ ሕዝቡን ሁሉ ማርካ ለኤዶም ሸጣለችና። ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በጢሮስ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ።”
አሞጽ 1:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፥ የእረኞችም ማሰማርያዎች ያለቅሳሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ገለዓድን በብረት መንኰራኵር አሂዶአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በአዛሄል ቤት እሳትን እሰድዳለሁ፥ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች። የደማስቆንም መወርወሪያ እሰብራለሁ፥ ተቀማጮችንም ከአዌን ሸለቆ አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፥ የሶርያም ሕዝብ ወደ ቂር ይማርካል፥ ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለኤዶምያስ አሳልፈው ይሰጡአቸው ዘንድ ምርኮኞችን ሁሉ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። ተቀማጮችን ከአዛጦን አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፥ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምርኮኞችን ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች።
አሞጽ 1:2-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሞጽ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ሆኖ እንደሚያገሣ አንበሳ የሚያስፈራ ድምፁን ያሰማል፤ ቃሉም ከኢየሩሳሌም ያስተጋባል፤ እረኞች መንጋ የሚያሰማሩበት መስክ ይጠወልጋል፤ በቀርሜሎስ ተራራ የሚገኘውም ልምላሜ ይደርቃል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የደማስቆ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የገለዓድን ሕዝብ የብረት ጥርስ ባለው መንኰራኲር አበራይተው አሠቃይተዋቸዋል። በንጉሥ ሐዛኤል ቤተ መንግሥት ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ እሳቱም ንጉሥ ቤንሀዳድ የሠራቸውንም ምሽጎች ያቃጥላል። የደማስቆን ከተማ የቅጽር በር መዝጊያ ሁሉ እሰባብራለሁ፤ በአዌን ሸለቆ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የቤትዔደንን መሪ አስወግዳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይወሰዳሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የጋዛ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የሀገሩን ሕዝብ ሁሉ ከማረኩ በኋላ ለኤዶም ሰዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። ስለዚህ በጋዛ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ በአሽዶድ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የአስቀሎናን መሪ አጠፋለሁ፤ የዔቅሮን ከተማ ኗሪዎችንም እቀጣለሁ፤ የተረፉትም ፍልስጥኤማውያን ይሞታሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የጢሮስ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ የገቡበትን የወንድምነት ቃል ኪዳን አፍርሰው የማረኳቸውን ሕዝቦች ለኤዶም አሳልፈው ሰጥተዋል፤ ስለዚህ በጢሮስ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል።”
አሞጽ 1:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም አለ፦ “ጌታ በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ድምፁን ያስተጋባል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ይጠወልጋሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ገለዓድን የብረት ጥርስ ባለው መውቅያ አበራይተውታልና ስለ ሦስት የደማስቆ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በአዛሄልም ቤት ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የአዴርንም ልጅ የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። የደማስቆንም መቀርቀሪያ እሰብራለሁ፥ ነዋሪዎችዋንም ከአዌን ሸለቆ፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይሄዳሉ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ለኤዶምያስ አሳልፈው ለመስጠት መላውን ሕዝብ ማርከው ወስደዋልና ስለ ሦስት የጋዛ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። ነዋሪዎችዋን ከአዛጦን፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በምርኮ የሄዱትን ሕዝብ ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድማማቾችንም ቃል ኪዳን አላስታወሱምና ስለ ሦስት የጢሮስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።”