ሐዋርያት ሥራ 8:5-25
ሐዋርያት ሥራ 8:5-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወረደ፤ ስለ ክርስቶስም ሰበከላቸው። ሕዝቡም የነገራቸውን በሰሙና ያደርገው የነበረውን ተአምራት በአዩ ጊዜ በአንድ ልብ የፊልጶስን ነገር ተቀበሉ። ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸውም ብዙዎች ነበሩና፥ በታላቅ ቃል እየጮኹ ይወጡ ነበር፤ ብዙዎች ልምሾዎችና አንካሶችም ይፈወሱ ነበር። በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። በዚያችም ከተማ ሲሞን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ የሰማርያ ሰዎችንም ያስት ነበር፤ ሰውየዉ ሥራየኛ ነበር፤ ራሱንም ታላቅ ያደርግ ነበር። ከታናናሾቹም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኀይል ይህ ነው” እያሉ ሁሉም ያደምጡት ነበር። ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላው ያታልላቸው ስለ ነበር ያዳምጡት ነበር። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብኮላቸው በአመኑ ጊዜ ሴቶችም ወንዶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ወዲያውኑ አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ይከተል ጀመር፤ በፊልጶስም እጅ የሚደረገውን ተአምርና ታላቅ ኀይል ባየ ጊዜ ይደነቅ ነበር። በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትም የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኩላቸው። ወርደውም መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጸለዩላቸው። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ እንጂ ከመካከላቸው በአንዱ ላይ ስንኳ መንፈስ ቅዱስ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያ ጊዜም እጃቸውን ጫኑባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በጫኑበት ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድ ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና፥ “እጄን በምጭንበት ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ዘንድ ለእኔም ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አላቸው። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፥ “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ልትገዛ ዐስበሃልና ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። በዚህ ነገር ዕድልና ርስት የለህም፥ በእግዚአብሔር ፊት ልብህ የቀና አይደለምና። አሁንም ከክፋትህ ተመለስና ንስሓ ግባ። የልቡናህንም ዐሳብ ይተውልህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ለምን። በመራራ መርዝ ተመርዘህ፥ በዐመፃ ማሰሪያ ተተብትበህ የምትኖር ሆነህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ፥ “ካላችሁት ሁሉ ምንም እንዳይደርስብኝ እናንተ ወደ እግዚአብሔር ለምኑልኝ” አለ። እነርሱም ከመሰከሩና የእግዚአብሔርን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በብዙዎች የሰማርያ መንደሮችም የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ።
ሐዋርያት ሥራ 8:5-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፊልጶስም ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ታምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና ዐንካሶችም ተፈወሱ፤ ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር። ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ “ይህ ሰው ‘ታላቁ ኀይል’ በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው” በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር፤ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ሥራው ስላስገረማቸውም ትኵረት ሰጥተው ይከተሉት ነበር። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሰበከላቸውን አምነው በመቀበላቸው ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ፤ ራሱ ሲሞን እንኳ ሳይቀር አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ተከትሎ ሄደ፤ የሚደረገውን ምልክትና ታላቅ ታምራት አይቶም ተገረመ። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኳቸው። እነርሱም ሰማርያ በደረሱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ለሰማርያ ሰዎች ጸለዩላቸው፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ ገና መንፈስ ቅዱስ በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በሚጭኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ አይቶ፣ ገንዘብ አመጣላቸውና እንዲህ አላቸው፤ “እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ።” ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለመግዛት አስበሃልና፣ አንተም ገንዘብህም አብራችሁ ጥፉ! ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ፣ አንተ በዚህ አገልግሎት ድርሻ ወይም ዕድል ፈንታ የለህም። አሁንም ስለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ወደ ጌታም ጸልይ፤ ምናልባት ይህን የልብህን ሐሳብ ይቅር ይልህ ይሆናል፤ ምክንያቱም በመራራነት ተሞልተህ፣ በዐመፅ ሰንሰለት ተይዘህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችሁት ምንም ነገር እንዳይደርስብኝ ጌታን ለምኑልኝ” አላቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስም የጌታን ቃል ከመሰከሩና ገልጠው ከተናገሩ በኋላ፣ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እየሰበኩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ሐዋርያት ሥራ 8:5-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። ርኵሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን፦ “እኔ ታላቅ ነኝ” ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ፦ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው” እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር። ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር። ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ። በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና፦ “እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ፦ “ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ” አላቸው። እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ።
ሐዋርያት ሥራ 8:5-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ሄዶ ሰዎቹን ስለ መሲሕ አስተማራቸው። ሰዎቹም የፊልጶስን ቃል በሰሙና የሚያደርጋቸውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በአንድ ሐሳብ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ይድኑ ነበር። ስለዚህ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። በዚያች ከተማ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በከተማይቱ ውስጥ አስማት እያደረገ የሰማርያን ሕዝብ ሲያስደንቅ ቈይቶአል፤ “እኔ ትልቅ ሰው ነኝ!” እያለም ይናገር ነበር። ሰዎች ሁሉ ትንሹም ትልቁም “ይህ ሰው ታላቅ ተብሎ የሚጠራው የእግዚአብሔር ኀይል ነው!” እያሉ በጥንቃቄ ያዳምጡት ነበር። በጥንቃቄ ያዳምጡት የነበረውም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ያስደንቃቸው ስለ ነበረ ነው። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተናገረውን መልካም ዜና በሰሙ ጊዜ ወንዶችም ሴቶችም አምነው ተጠመቁ። ስምዖን እንኳን ሳይቀር አምኖ ተጠመቀና ከፊልጶስ ጋር ተባባሪ ሆነ፤ የሚደረጉትንም ድንቅ ነገሮችና ታላላቅ ተአምራት በማየቱ ይገረም ነበር። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሰማርያ ላኩአቸው። ስለዚህ የሰማርያ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሄደው ጸለዩላቸው። የሰማርያ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ መንፈስ ቅዱስ ገና በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ፥ እጆቻቸውን በጫኑባቸው ጊዜ ሰዎቹ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ሐዋርያት እጆቻቸውን ሲጭኑባቸው መንፈስ ቅዱስ ለሰዎቹ መሰጠቱን ስምዖን ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና፥ “እኔም እጄን የምጭንበት ሰው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለማግኘት በማሰብህ ገንዘብህ ካንተ ጋር ይጥፋ! ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ አንተ ከዚህ ነገር ክፍል ወይም ዕጣ የለህም። እንግዲህ ከዚህ ከክፋትህ ተጸጽተህ ንስሓ ግባ፤ ምናልባት የልብህን ክፉ አሳብ ይቅር ይልልህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ለምን። አንተ በመራራ ቅናት እንደ ተሞላህና የኃጢአት እስረኛ እንደ ሆንክ አያለሁ።” ስምዖንም “አሁን ከተናገራችሁት አንዳች እንኳን እንዳይደርስብኝ እናንተው ራሳችሁ ወደ ጌታ ጸልዩልኝ” አላቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ከመሰከሩና የጌታንም ቃል ከተናገሩ በኋላ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እያበሠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ሐዋርያት ሥራ 8:5-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። ርኩሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን “እኔ ታላቅ ነኝ፤” ብሎ፥ እየጠነቆለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው፤” እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር። ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቆላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር። ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ። በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና “እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ፤” አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፤ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዐመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ “ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ፤” አላቸው። እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ።