ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወረደ፤ ስለ ክርስቶስም ሰበከላቸው። ሕዝቡም የነገራቸውን በሰሙና ያደርገው የነበረውን ተአምራት በአዩ ጊዜ በአንድ ልብ የፊልጶስን ነገር ተቀበሉ። ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸውም ብዙዎች ነበሩና፥ በታላቅ ቃል እየጮኹ ይወጡ ነበር፤ ብዙዎች ልምሾዎችና አንካሶችም ይፈወሱ ነበር። በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። በዚያችም ከተማ ሲሞን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ የሰማርያ ሰዎችንም ያስት ነበር፤ ሰውየዉ ሥራየኛ ነበር፤ ራሱንም ታላቅ ያደርግ ነበር። ከታናናሾቹም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኀይል ይህ ነው” እያሉ ሁሉም ያደምጡት ነበር። ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላው ያታልላቸው ስለ ነበር ያዳምጡት ነበር። ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብኮላቸው በአመኑ ጊዜ ሴቶችም ወንዶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ወዲያውኑ አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ይከተል ጀመር፤ በፊልጶስም እጅ የሚደረገውን ተአምርና ታላቅ ኀይል ባየ ጊዜ ይደነቅ ነበር። በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትም የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኩላቸው። ወርደውም መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጸለዩላቸው። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ እንጂ ከመካከላቸው በአንዱ ላይ ስንኳ መንፈስ ቅዱስ ገና አልወረደም ነበርና። በዚያ ጊዜም እጃቸውን ጫኑባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በጫኑበት ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድ ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና፥ “እጄን በምጭንበት ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ዘንድ ለእኔም ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አላቸው። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፥ “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ልትገዛ ዐስበሃልና ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። በዚህ ነገር ዕድልና ርስት የለህም፥ በእግዚአብሔር ፊት ልብህ የቀና አይደለምና። አሁንም ከክፋትህ ተመለስና ንስሓ ግባ። የልቡናህንም ዐሳብ ይተውልህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ለምን። በመራራ መርዝ ተመርዘህ፥ በዐመፃ ማሰሪያ ተተብትበህ የምትኖር ሆነህ አይሃለሁና።” ሲሞንም መልሶ፥ “ካላችሁት ሁሉ ምንም እንዳይደርስብኝ እናንተ ወደ እግዚአብሔር ለምኑልኝ” አለ። እነርሱም ከመሰከሩና የእግዚአብሔርን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በብዙዎች የሰማርያ መንደሮችም የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ።
የሐዋርያት ሥራ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 8:5-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos