ሐዋርያት ሥራ 3:11-26
ሐዋርያት ሥራ 3:11-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጴጥሮስና ዮሐንስም ይዘውት ወደ መቅደስ ሲገቡ ሕዝቡ ሁሉ ደንግጠው ወደ ሰሎሞን መመላለሻ ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም ሕዝቡን ባያቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ለምን ታደንቃላችሁ? እኛንስ በኀይላችንና በጽድቃችን ይህን ሰው በእግሩ እንዲሄድ እንዳደረግነው አስመስላችሁ ለምን ታዩናላችሁ? የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ፥ የአባቶቻችንም አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትን፥ እርሱም ሊተወው ወዶ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ልጁን ኢየሱስን ገለጠው። እናንተ ግን ቅዱሱንና ጻድቁን ካዳችሁት፤ ነፍሰ ገዳዩን ሰውም እንዲያድንላችሁ ለመናችሁ። የሕይወትን ባለቤት ግን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ምስክሮቹ ነን። ስሙን በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፤ እርሱንም በማመን በፊታችሁ ይህን ሕይወት ሰጠው። “አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረ እንዲሁ ፈጸመ። እንግዲህ ኀጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ ንስሓ ግቡ፥ ተመለሱም። ከእግዚአብሔር ዘንድም የይቅርታ ዘመን ይመጣል። አስቀድሞ የመረጠውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ይልክላችኋል። እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እስከ ተናገረው የመደራጀት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባል። ሙሴም አባቶቻችንን እንዲህ ብሎአቸዋል፦ እግዚአብሔር አምላካችን ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙት። ያን ነቢይ የማትሰማው ነፍስም ሁሉ ከወገኖችዋ ተለይታ ትጥፋ። ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀኖች ተናግረዋል፤ አስተምረዋልም። እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በሠራው ሥርዐትም የተወለዳችሁ ናችሁ፤ ለአብርሃም፦ ‘በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎታልና። እግዚአብሔርም አስቀድሞ ልጁን አስነሣላችሁ፤ ሁላችሁም ከክፋታችሁ እንድትመለሱ ይባርካችሁ ዘንድ ላከው።”
ሐዋርያት ሥራ 3:11-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የተፈወሰውም ሰው ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋራ ጥብቅ ብሎ ዐብሯቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደ ነበሩበት “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ። ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቍጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ? የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በርሱ ፊት ካዳችሁት፤ ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤ የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን። ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው የበረታው በኢየሱስ ስም በማመን ነው፤ ሁላችሁም እንደምታዩት ፍጹም ፈውስ እንዲያገኝ ያደረገው የኢየሱስ ስምና በርሱ አማካይነት የሚገኘው እምነት ነው። “አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን የርሱ የሆነው ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የተናገረውን ፈጽሟል። እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን፣ እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል። እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፣ ሁሉን ነገር እስከሚያድስበት ዘመን ድረስ እርሱ በሰማይ ይቈይ ዘንድ ይገባል። ሙሴም እንዲህ ብሏል፤ ‘ጌታ አምላካችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙት፤ ያን ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይታ ትጥፋ።’ “በርግጥም ከሳሙኤል ጀምሮ የተነሡት ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ጊዜያት ተናግረዋል። እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ የገባው ኪዳን ወራሾች ናችሁ። እግዚአብሔር ብላቴናውን ባስነሣ ጊዜ፣ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ መልሶ ይባርካችሁ ዘንድ አስቀድሞ ወደ እናንተ ላከው።”
ሐዋርያት ሥራ 3:11-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ? የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፥ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞም በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና። ሙሴም ለአባቶች፦ ‘ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች’ አለ። ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ። እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም፦ ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።”
ሐዋርያት ሥራ 3:11-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዳነው ሰው ከጴጥሮስና ከዮሐንስ አልለይም በማለት ይዞአቸው ሳለ ሰዎቹ ተደንቀው “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደሚባለው ስፍራ ወደ እነርሱ ሮጠው ሄዱ፤ ጴጥሮስም ሰዎቹን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ነገር ስለምን ትደነቃላችሁ? ስለምንስ ትኲር ብላችሁ ታዩናላችሁ? እኛ በራሳችን ኀይል ወይም በራሳችን መልካም ሥራ ይህን ሰው እንዲራመድ ያደረግነው ይመስላችኋልን? የአባቶቻችን የአብርሃም፥ የይስሐቅና፥ የያዕቆብ አምላክ ልጁን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እርሱን በጲላጦስ ፊት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስም ሊለቀው ቢፈልግ እንኳ ‘አንፈልግም’ አላችሁ። እናንተ ቅዱሱንና ጻድቁን ‘አንፈልገውም’ ብላችሁ አንድ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ። ሕይወት ሰጪ የሆነውንም ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን። ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው ድኖ የበረታው በኢየሱስ ስም በተገኘው እምነት ነው፤ በኢየሱስ ስም በማመኑም በሁላችሁ ፊት ሙሉ ጤንነት አግኝቶአል። “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ላይ ያደረጋችኹትን ነገር እናንተም እንዳለቆቻችሁ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ ‘መሲሑ መከራ መቀበል አለበት’ ያለው ቃል በዚህ ዐይነት እንዲፈጸም አደረገ። እንግዲህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስላችሁ ንስሓ ገብታችሁ ወደ ጌታ ተመለሱ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ የምትታደሱበት ዘመን ይመጣላችኋል፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእናንተ የመረጠውን መሲሕ ኢየሱስን ይልክላችኋል። እርሱም በሰማይ የሚቈየው እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው ዓለም ሁሉ እስኪታደስ ድረስ ነው። ሙሴም እንዲህ ብሎአል፦ ‘ጌታ አምላክህ እኔን እንዳስነሣኝ እንዲሁ ከወንድሞቻችሁ መካከል ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙ፤ ያን ነቢይ የማይሰማ ሁሉ ከሕዝብ ተለይቶ ፈጽሞ ይጠፋል።’ ቀጥሎም ከሳሙኤል ጀምሮ የነበሩ ነቢያት ሁሉ፥ ስለዚህ ዘመን እንዲሁ ተናግረዋል። እናንተ የነቢያት ወራሾች ናችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር ልጁን የላከው በመጀመሪያ ለእናንተ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው እያንዳንዳችሁን ከክፉ መንገዳችሁ በመመለስ እንዲባርካችሁ ነው።”
ሐዋርያት ሥራ 3:11-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ስለምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኀይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ? የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቆርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፤ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፤ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። “አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞም በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኀጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም። እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና። ሙሴም ለአባቶች ‘ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች፤’ አለ። ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ። እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ፤’ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ ላከው።”