ጴጥሮስና ዮሐንስም ይዘውት ወደ መቅደስ ሲገቡ ሕዝቡ ሁሉ ደንግጠው ወደ ሰሎሞን መመላለሻ ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም ሕዝቡን ባያቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ለምን ታደንቃላችሁ? እኛንስ በኀይላችንና በጽድቃችን ይህን ሰው በእግሩ እንዲሄድ እንዳደረግነው አስመስላችሁ ለምን ታዩናላችሁ? የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ፥ የአባቶቻችንም አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትን፥ እርሱም ሊተወው ወዶ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ልጁን ኢየሱስን ገለጠው። እናንተ ግን ቅዱሱንና ጻድቁን ካዳችሁት፤ ነፍሰ ገዳዩን ሰውም እንዲያድንላችሁ ለመናችሁ። የሕይወትን ባለቤት ግን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ምስክሮቹ ነን። ስሙን በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፤ እርሱንም በማመን በፊታችሁ ይህን ሕይወት ሰጠው። “አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረ እንዲሁ ፈጸመ። እንግዲህ ኀጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ ንስሓ ግቡ፥ ተመለሱም። ከእግዚአብሔር ዘንድም የይቅርታ ዘመን ይመጣል። አስቀድሞ የመረጠውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ይልክላችኋል። እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እስከ ተናገረው የመደራጀት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባል። ሙሴም አባቶቻችንን እንዲህ ብሎአቸዋል፦ እግዚአብሔር አምላካችን ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙት። ያን ነቢይ የማትሰማው ነፍስም ሁሉ ከወገኖችዋ ተለይታ ትጥፋ። ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀኖች ተናግረዋል፤ አስተምረዋልም። እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በሠራው ሥርዐትም የተወለዳችሁ ናችሁ፤ ለአብርሃም፦ ‘በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎታልና። እግዚአብሔርም አስቀድሞ ልጁን አስነሣላችሁ፤ ሁላችሁም ከክፋታችሁ እንድትመለሱ ይባርካችሁ ዘንድ ላከው።”
የሐዋርያት ሥራ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 3:11-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች