የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 26:1-29

ሐዋርያት ሥራ 26:1-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አግ​ሪ​ጳም ጳው​ሎ​ስን፥ “ስለ ራስህ ትና​ገር ዘንድ ፈቅ​ደ​ን​ል​ሃል” አለው፤ ከዚ​ህም በኋላ ጳው​ሎስ እጁን አነ​ሣና ይነ​ግ​ራ​ቸው ጀመር፤ እን​ዲ​ህም አለ፦ “ንጉሥ አግ​ሪጳ ሆይ፥ አይ​ሁድ እኔን ስለ ከሰ​ሱ​በት ነገር ሁሉ ዛሬ በአ​ንተ ዳኝ​ነት እከ​ራ​ከር ዘንድ ስለ ተገ​ባኝ ራሴን እንደ ተመ​ሰ​ገነ አድ​ርጌ እቈ​ጥ​ረ​ዋ​ለሁ። የአ​ይ​ሁ​ድን ጠባ​ያ​ቸ​ው​ንና ክር​ክ​ራ​ቸ​ውን አጥ​ብ​ቀህ ታው​ቃ​ለ​ህና ታግ​ሠህ ታደ​ም​ጠኝ ዘንድ እለ​ም​ን​ሃ​ለሁ። “ከል​ጅ​ነቴ ጀምሮ በወ​ገ​ኖች መካ​ከል በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም የኖ​ር​ሁ​ትን ኑሮ አይ​ሁድ ሁሉ ያው​ቃሉ። ሊመ​ሰ​ክ​ሩም ከወ​ደዱ እኔ ፈሪ​ሳዊ ሆኜ በአ​ባ​ቶ​ቻ​ችን ሕግ እን​ደ​ም​ኖር ከጥ​ንት ጀምሮ እነ​ርሱ ያው​ቁ​ል​ኛል። አሁ​ንም ከጥ​ንት ጀምሮ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ለአ​ባ​ቶ​ቻ​ችን የተ​ሰ​ጠ​ውን ተስፋ በመ​ታ​መን ከፍ​ርድ በታች ቆሜ​አ​ለሁ። ንጉሥ አግ​ሪጳ ሆይ፥ ዐሥራ ሁለቱ ነገ​ዶ​ቻ​ችን በመ​ዓ​ል​ትም በሌ​ሊ​ትም እር​ሱን እያ​ገ​ለ​ገሉ ወደ እር​ስዋ ይደ​ርሱ ዘንድ ተስፋ ያደ​ር​ጋሉ፤ አይ​ሁ​ድም የሚ​ከ​ስ​ሱኝ ስለ​ዚህ ተስፋ ነው። እን​ዴ​ትስ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሙታ​ንን እን​ደ​ሚ​ያ​ስ​ነ​ሣ​ቸው በእ​ና​ንተ ዘንድ የማ​ይ​ታ​መን ሆኖ ይቈ​ጠ​ራል? “እኔም ብዙ ጊዜ በና​ዝ​ሬቱ በኢ​የ​ሱስ ስም ላይ ክፉ ነገር ላደ​ርግ ቈርጬ ነበር። ይህ​ንም በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም አደ​ረ​ግ​ሁት፤ ከሊ​ቃነ ካህ​ና​ትም ሥል​ጣን ተቀ​ብዬ ከቅ​ዱ​ሳን ብዙ​ዎ​ችን ወደ ወኅኒ ቤት አስ​ገ​ባ​ኋ​ቸው፤ ሲገ​ድ​ሏ​ቸ​ውም አብሬ እመ​ክር ነበ​ርሁ። በየ​ም​ኵ​ራቡ ሁሉ የማ​ስ​ገ​ደጃ ማዘዣ አም​ጥቼ፥ በግድ የኢ​የ​ሱ​ስን ስም እን​ዲ​ሰ​ድቡ ዘወ​ትር መከራ አጸ​ና​ባ​ቸው ነበር፤ ይል​ቁ​ንም ወደ ሌሎች ከተ​ማ​ዎች እያ​ሳ​ደ​ድሁ ከፋ​ሁ​ባ​ቸው። “ይህ​ንም ለመ​ፈ​ጸም ከሊ​ቃነ ካህ​ናት ሥል​ጣን ተቀ​ብዬ ወደ ደማ​ስቆ ከተማ ሄድሁ። ንጉሥ ሆይ፥ እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመ​ን​ገድ ስሄድ ከፀ​ሐይ ይልቅ የሚ​በራ መብ​ረቅ በእ​ኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነ​በ​ሩት ላይ ከሰ​ማይ ሲያ​ን​ፀ​ባ​ርቅ አየሁ። ሁላ​ች​ንም በም​ድር ላይ በወ​ደ​ቅን ጊዜ በዕ​ብ​ራ​ይ​ስጥ ቋንቋ፦ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳ​ድ​ደ​ኛ​ለህ? በሾለ ብረት ላይ መር​ገጥ ለአ​ንተ ይብ​ስ​ሃል’ የሚ​ለ​ኝን ቃል ሰማሁ። እኔም፦ ‘አቤቱ አንተ ማነህ?’ አልሁ፤ ጌታም አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የም​ታ​ሳ​ድ​ደኝ ኢየ​ሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነ​ሣና በእ​ግ​ርህ ቁም፤ እኔን ባየ​ህ​በ​ትና ወደ​ፊ​ትም በም​ታ​ይ​በት ነገር አገ​ል​ጋ​ይና ምስ​ክር አድ​ርጌ ልሾ​ምህ ስለ​ዚህ ተገ​ል​ጬ​ል​ሃ​ለ​ሁና። እኔም ከሕ​ዝ​ቡና ወደ እነ​ርሱ ከም​ል​ክህ ከአ​ሕ​ዛብ አድ​ን​ሃ​ለሁ። ይኸ​ውም ዐይ​ና​ቸ​ውን ትከ​ፍ​ት​ላ​ቸው ዘንድ፥ ከጨ​ለ​ማም ወደ ብር​ሃን፥ ሰይ​ጣ​ንን ከማ​ም​ለ​ክም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትመ​ል​ሳ​ቸው ዘንድ፥ ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ውም ይሰ​ረ​ይ​ላ​ቸው ዘንድ፥ በስ​ሜም በማ​መን ከቅ​ዱ​ሳን ጋር አን​ድ​ነ​ትን ያገኙ ዘንድ ነው።’ “አሁ​ንም ንጉሥ አግ​ሪጳ ሆይ፥ ከሰ​ማይ የተ​ገ​ለ​ጠ​ል​ኝን ራእይ አል​ካ​ድ​ሁም። አስ​ቀ​ድሜ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምና በደ​ማ​ስቆ ላሉት፥ ለይ​ሁዳ አው​ራ​ጃ​ዎ​ችም ሁሉ ነገ​ር​ኋ​ቸው፤ ለአ​ሕ​ዛ​ብም ንስሓ ገብ​ተው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ለሱ ዘንድ፥ ለን​ስ​ሓ​ቸ​ውም የሚ​ገባ ሥራን ይሠሩ ዘንድ አስ​ተ​ማ​ር​ኋ​ቸው። ሰለ​ዚ​ህም ብቻ አይ​ሁድ በመ​ቅ​ደስ ያዙኝ፤ ሊገ​ድ​ሉ​ኝም ወደዱ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አዳ​ነ​ኝና ለታ​ላ​ቁም፥ ለታ​ና​ሹም እየ​መ​ሰ​ከ​ርሁ እስከ ዛሬ ደረ​ስሁ፤ ይደ​ረግ ዘንድ ካለው፥ ነቢ​ያት ከተ​ና​ገ​ሩት፥ ሙሴም ከተ​ና​ገ​ረው ሌላ ያስ​ተ​ማ​ር​ሁት የለም። ክር​ስ​ቶስ እን​ደ​ሚ​ሞት፥ ከሙ​ታን ተለ​ይ​ቶም አስ​ቀ​ድሞ እን​ደ​ሚ​ነሣ፥ ለሕ​ዝ​ብና ለአ​ሕ​ዛብ ሁሉ፥ ለመ​ላ​ውም ዓለም እን​ደ​ሚ​ያ​በራ።” ይህ​ንም ስለ ራሱ ሲና​ገር ሀገረ ገዢው ፊስ​ጦስ መለሰ፤ ድም​ፁ​ንም ከፍ አድ​ርጎ፥ “ጳው​ሎስ ሆይ፥ ልታ​ብድ ነውን? ብዙ ትም​ህ​ርት እኮ ልብን ይነ​ሣል” አለው። ጳው​ሎ​ስም እን​ዲህ አለው፥ “ክቡር ፊስ​ጦስ ሆይ፥ እው​ነ​ትና የተ​ጣራ ነገ​ርን እና​ገ​ራ​ለሁ እንጂ ዕብ​ደ​ትስ የለ​ብ​ኝም። በፊቱ ገልጬ የም​ና​ገ​ር​ለት እርሱ ራሱ ንጉሥ አግ​ሪጳ ያው​ቅ​ል​ኛል፤ ከዚ​ህም የሚ​ሳ​ተው ነገር ያለ አይ​መ​ስ​ለ​ኝም፤ ወደ ጎን የተ​ሰ​ወረ አይ​ደ​ለ​ምና። ንጉሥ አግ​ሪጳ ሆይ፥ እነሆ፥ በነ​ቢ​ያት ቃል ታም​ና​ለ​ህን? እን​ደ​ም​ታ​ም​ንም አው​ቃ​ለሁ።” አግ​ሪ​ጳም ጳው​ሎ​ስን፥ “አሁ​ንስ ወደ ክር​ስ​ቲ​ያ​ን​ነት ልታ​ገ​ባኝ ጥቂት ብቻ ቀር​ቶ​ሃል” አለው። ጳው​ሎ​ስም፥ “በጥ​ቂ​ትም ቢሆን፥ በብ​ዙም ቢሆን አንተ ብቻ ሳት​ሆን ዛሬ የሚ​ሰ​ሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ ከእ​ስ​ራቴ በቀር እንደ እኔ እን​ዲ​ሆኑ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እጸ​ል​ያ​ለሁ።”

ሐዋርያት ሥራ 26:1-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አግሪጳም ጳውሎስን፣ “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መከላከያውን አቀረበ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ አይሁድ በእኔ ላይ ላቀረቡት ክስ ሁሉ ዛሬ በፊትህ የመከላከያ መልስ ለማቅረብ በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቈጥረዋለሁ፤ ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ። “ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በአገሬም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደ ኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ ደግሞም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለሚያውቁኝ ከሃይማኖታችን እጅግ ጥብቅ በሆነው ወገን ውስጥ ሆኜ እንደ አንድ ፈሪሳዊ መኖሬን ሊመሰክሩ ፈቃደኞች ከሆኑ ቃላቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። አሁንም ተከስሼ እዚህ የቀረብሁበት ምክንያት፣ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ቃል የገባውን ነገር ተስፋ በማድረጌ ነው። ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ከልብ እያገለገሉ፣ ሲፈጸም ለማየት የሚተጉለትም ተስፋ ይኸው ነው። ንጉሥ ሆይ፤ አይሁድም የሚከስሱኝ ስለዚሁ ተስፋ ነው። ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሣት እንደማይችል አድርጋችሁ የምትቈጥሩት ለምንድን ነው? “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም በምችለው መንገድ ሁሉ መቃወም እንዳለብኝ ወስኜ ነበር። በኢየሩሳሌምም ያደረግሁት ይህንኑ ነበር፤ ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብዬ ብዙ ቅዱሳንን አሳስሬአለሁ፤ በመገደላቸውም ተስማምቻለሁ፤ ላስቀጣቸውም ብዙ ጊዜ ከምኵራብ ምኵራብ እየተዘዋወርሁ፣ የስድብ ቃል እንዲናገሩ አስገድዳቸው ነበር፤ በቍጣም ተሞልቼ በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትዬ አሳደድኋቸው። “በዚህ መሠረት አንድ ቀን ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ በምጓዝበት ጊዜ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እኩለ ቀን ላይ በመንገድ ሳለሁ፣ ብሩህነቱ ከፀሓይ የሚበልጥ ብርሃን በእኔና በባልንጀሮቼ ዙሪያ ከሰማይ ሲያበራ አየሁ፤ ሁላችንም በምድር ላይ ወደቅን፤ እኔም በዕብራይስጥ ቋንቋ፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን ብትጋፋ ጕዳቱ በአንተ ይብሳል’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ ” አልሁ። “ጌታም እንዲህ አለኝ፤ ‘እኔ፣ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። አሁንም፣ ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለ እኔ ስላየኸውና ወደ ፊትም ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምስክር እንድትሆን ልሾምህ ተገልጬልሃለሁ። ከገዛ ሕዝብህና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ፤ አንተም ዐይናቸውን ትከፍታለህ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ።’ “እንግዲህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ከሰማይ ለታየኝ ራእይ አልታዘዝ አላልሁም፤ ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ። አይሁድም በመቅደስ ይዘው ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚሁ ምክንያት ነው። የእግዚአብሔር ርዳታ እስከ ዛሬ ስላልተለየኝ፣ እነሆ፤ እዚህ ቆሜ ለትንሹም ለትልቁም እመሰክራለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆናል፣ ይፈጸማል ካሉት በስተቀር አንዳች ነገር አልተናገርሁም፤ ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።” ፊስጦስም የጳውሎስን ንግግር እዚህ ላይ በማቋረጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አእምሮህን ስተሃል፤ የትምህርትህም ብዛት አሳብዶሃል” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፤ የምናገረው እውነተኛና ትክክለኛ ነገር እንጂ እብድስ አይደለሁም። ይህን የምናገረውን ነገር ንጉሡ ያውቀዋልና፤ በፊቱ በልበ ሙሉነት እናገራለሁ፤ ደግሞም በድብቅ የተደረገ ነገር ባለመኖሩ፣ ከዚህ ነገር አንድም እንደማይሰወርበት ርግጠኛ ነኝ። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ነቢያትን ታምን የለም ወይ? አዎን፤ እንደምታምን ዐውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፣ “እንዲህ በቀላሉ ክርስቲያን የምታደርገኝ ይመስልሃልን?” አለው። ጳውሎስም፣ “በቀላሉም ሆነ በብዙ፣ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ፣ ከዚህ ከታሰርሁበት ሰንሰለት በስተቀር፣ እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” አለ።

ሐዋርያት ሥራ 26:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አግሪጳም ጳውሎስን፦ “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ መለሰ እንዲህ ሲል፦ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ ሊመሰክሩ ይወዱ እንደ ሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና። አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል? እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቈጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር። ስለዚህም ነገ ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ፦ “ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ። እኔም፦ “ጌታ ሆይ፥ ማንነህ?” አልሁ። እርሱም አለኝ፦ “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።” ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ። ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።” እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ፦ “ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፦ “በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ” አለው። ጳውሎስም፦ “በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራቴ በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ” አለው።

ሐዋርያት ሥራ 26:1-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አግሪጳ ጳውሎስን “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው፤ ጳውሎስም እጁን ዘረጋና እንዲህ ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ። “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! አይሁድ በከሰሱኝ ነገር ሁሉ ዛሬ በአንተ ፊት የመከላከያ መልስ ስሰጥ እጅግ ደስ ይለኛል። በተለየም አንተ የአይሁድን ሥርዓትና ክርክር ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህ፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታዳምጠኝ እለምንሃለሁ። “ከልጅነቴ ጀምሮ እንዴት እንደ ኖርኩ አይሁድ ያውቃሉ፤ ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከልና በኢየሩሳሌም የኖርኩትን ሕይወቴን ያውቁታል። ደግሞም ሊመሰክሩ ቢፈቅዱ ከሃይማኖታችን በጣም ወግ አጥባቂ ከሆነው ክፍል ፈሪሳዊ ሆኜ እንደ ኖርኩ ከመጀመሪያው አንሥቶ ያውቃሉ። አሁን ግን ለፍርድ እዚህ የቆምኩት እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ስለ ሰጠው የቃል ኪዳን ተስፋ ነው። ወደዚህ ተስፋ ለመድረስ ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን እግዚአብሔርን ሌት ተቀን እያመለኩ ይጠባበቁ ነበር፤ ንጉሥ ሆይ! እኔም በአይሁድ የተከሰስኩበት በዚህ ተስፋ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ መሆኑ ስለምን በእናንተ ዘንድ ሊታመን የማይቻል ሆነ? “እኔ ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የተቻለኝን ያኽል መቃወም አለብኝ ብዬ አስብ ነበር። በኢየሩሳሌም ያደረግኹትም ይህንኑ ነበር፤ ከካህናት አለቆች በተቀበልኩት ሥልጣን ከምእመናን ብዙዎቹ ወደ ወህኒ ቤት እንዲገቡ አድርጌአለሁ፤ ሲገድሉአቸውም ከገዳዮቻቸው ጋር ተስማምቻለሁ። ብዙ ጊዜ በየምኲራቡ እንዲቀጡና በጌታ ላይ የስድብ ቃል እንዲናገሩ አስገድዳቸው ነበር፤ በእነርሱ ላይ በጣም ተቈጥቼም ወደ ሌሎች የውጪ አገር ከተሞች እንኳ ወጥቼ እየሄድኩ አሳድዳቸው ነበር። “ለዚሁ ጉዳይ ከካህናት አለቆች ሙሉ ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ እጓዝ ነበር፤ ንጉሥ ሆይ! በመንገድ ሳለሁ ልክ እኩለ ቀን ሲሆን ከፀሐይ ብርሃን የሚበልጥ ብርሃን አየሁ፤ ይህም ብርሃን በእኔና ከእኔ ጋር በሚጓዙት ሰዎች ዙሪያ ከሰማይ አበራ። ሁላችንም በመሬት ላይ ወድቀን ሳለ በአይሁድ ቋንቋ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ? በሰይፍ ስለት ላይ ብትቆም ራስህን ትጐዳለህ’ የሚል ድምፅ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልኩ፤ ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። አሁን ግን ተነሥና በእግርህ ቁም፤ እኔ የተገለጥኩልህ አሁን እኔን ባየህበትና ወደፊትም እኔ ለአንተ በምገለጥበት ነገር አገልጋይና ምስክር እንድትሆነኝ ልሾምህ ፈልጌ ነው። ከእስራኤል ሕዝብና ወደ እነርሱ ከምልክህ አሕዛብ እጅ አድንሃለሁ። ዐይናቸውን እንድትከፍትላቸውና ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድታወጣቸው ከሰይጣንም ግዛት ወደ እግዚአብሔር እንድትመልሳቸው አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በእኔ በማመናቸው ምክንያት የኃጢአታቸውን ይቅርታ ያገኛሉ፤ በተመረጡት መካከልም ርስትን ይካፈላሉ።’ “ስለዚህ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ከሰማይ ለተሰጠኝ ራእይ እምቢተኛ አልሆንኩም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ያሉት ሰዎች፥ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ሁሉ ያሉት እንዲሁም አሕዛብ ጭምር ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ አስተማርኳቸው፤ ንስሓ መግባታቸውን የሚያመለክት ነገር እንዲያደርጉም አስተማርኳቸው። በዚህ ምክንያት አይሁድ በቤተ መቅደስ እንዳለሁ ያዙኝና ሊገድሉኝ ሞከሩ። እስከ ዛሬ ድረስ የእግዚአብሔር ርዳታ አልተለየኝም፤ ስለዚህ ለትንሹም ለትልቁም እየመሰከርኩ እዚህ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ አስቀድመው እንዲህ ይሆናል ያሉትን ከመናገር በቀር ሌላ ምንም አልተናገርኩም። እነርሱም የተናገሩት ‘መሲሕ መከራ ይቀበላል፤ ከሞት በመነሣትም የመጀመሪያ ሆኖ የመዳንን ብርሃን ለእስራኤል ሕዝብና ለአሕዛብ ይገልጣል’ ብለው ነው።” ጳውሎስ ይህን ሲናገር ሳለ ፊስጦስ “ጳውሎስ ሆይ! አሁንስ አበድክ፤ ብዙ መማርህ ወደ እብደት አድርሶሃል!” ሲል ጮኾ ተናገረ። ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እጅግ የተከበርክ ፊስጦስ ሆይ! እውነተኛውንና ትክክለኛውን ነገር እናገራለሁ እንጂ አላበድኩም። በፊቱ በግልጥ የተናገርኩት ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል። ይህም በስውር ያልተደረገ ስለ ሆነ ንጉሡ እንደሚረዳው እርግጠኛ ነኝ። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምን የለምን? እንደምታምን ዐውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፥ “አንተ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው እኮ” አለው። ጳውሎስም “በአጭር ጊዜም ይሁን በረጅም ጊዜ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ ንግግሬን የሰሙ ሁሉ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ እግዚአብሔርን እለምናለሁ!” አለ።

ሐዋርያት ሥራ 26:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አግሪጳም ጳውሎስን “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል፤” አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። “ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ ሊመሰክሩ ይወዱ እንደሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና። አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል ዐሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ከአይሁድ እከሰሳለሁ። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደሆነ ስለምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቆጠራል? “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፤ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቆጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር። “ስለዚህም ነገር ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ ንጉሥ ሆይ! በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል፤’ የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም አለኝ ‘አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዐይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።’ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሓ ይገቡ ዘንድና ለንስሓ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ተናገርሁ። ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ሞከሩ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።” እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ “ጳውሎስ ሆይ! አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል፤” አለው። ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ! የእውነትንና የአምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን “በጥቂት ጊዜ ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ፤” አለው። ጳውሎስም “በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራት በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ፤” አለው።