አግሪጳም ጳውሎስን፥ “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ፈቅደንልሃል” አለው፤ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጁን አነሣና ይነግራቸው ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አይሁድ እኔን ስለ ከሰሱበት ነገር ሁሉ ዛሬ በአንተ ዳኝነት እከራከር ዘንድ ስለ ተገባኝ ራሴን እንደ ተመሰገነ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። የአይሁድን ጠባያቸውንና ክርክራቸውን አጥብቀህ ታውቃለህና ታግሠህ ታደምጠኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። “ከልጅነቴ ጀምሮ በወገኖች መካከል በኢየሩሳሌም የኖርሁትን ኑሮ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ። ሊመሰክሩም ከወደዱ እኔ ፈሪሳዊ ሆኜ በአባቶቻችን ሕግ እንደምኖር ከጥንት ጀምሮ እነርሱ ያውቁልኛል። አሁንም ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን የተሰጠውን ተስፋ በመታመን ከፍርድ በታች ቆሜአለሁ። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን በመዓልትም በሌሊትም እርሱን እያገለገሉ ወደ እርስዋ ይደርሱ ዘንድ ተስፋ ያደርጋሉ፤ አይሁድም የሚከስሱኝ ስለዚህ ተስፋ ነው። እንዴትስ እግዚአብሔር ሙታንን እንደሚያስነሣቸው በእናንተ ዘንድ የማይታመን ሆኖ ይቈጠራል? “እኔም ብዙ ጊዜ በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም ላይ ክፉ ነገር ላደርግ ቈርጬ ነበር። ይህንም በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከሊቃነ ካህናትም ሥልጣን ተቀብዬ ከቅዱሳን ብዙዎችን ወደ ወኅኒ ቤት አስገባኋቸው፤ ሲገድሏቸውም አብሬ እመክር ነበርሁ። በየምኵራቡ ሁሉ የማስገደጃ ማዘዣ አምጥቼ፥ በግድ የኢየሱስን ስም እንዲሰድቡ ዘወትር መከራ አጸናባቸው ነበር፤ ይልቁንም ወደ ሌሎች ከተማዎች እያሳደድሁ ከፋሁባቸው። “ይህንም ለመፈጸም ከሊቃነ ካህናት ሥልጣን ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ከተማ ሄድሁ። ንጉሥ ሆይ፥ እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ ስሄድ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ። ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ፦ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? በሾለ ብረት ላይ መርገጥ ለአንተ ይብስሃል’ የሚለኝን ቃል ሰማሁ። እኔም፦ ‘አቤቱ አንተ ማነህ?’ አልሁ፤ ጌታም አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ እኔን ባየህበትና ወደፊትም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር አድርጌ ልሾምህ ስለዚህ ተገልጬልሃለሁና። እኔም ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ። ይኸውም ዐይናቸውን ትከፍትላቸው ዘንድ፥ ከጨለማም ወደ ብርሃን፥ ሰይጣንን ከማምለክም ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸው ዘንድ፥ ኀጢአታቸውም ይሰረይላቸው ዘንድ፥ በስሜም በማመን ከቅዱሳን ጋር አንድነትን ያገኙ ዘንድ ነው።’ “አሁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከሰማይ የተገለጠልኝን ራእይ አልካድሁም። አስቀድሜ በኢየሩሳሌምና በደማስቆ ላሉት፥ ለይሁዳ አውራጃዎችም ሁሉ ነገርኋቸው፤ ለአሕዛብም ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ፥ ለንስሓቸውም የሚገባ ሥራን ይሠሩ ዘንድ አስተማርኋቸው። ሰለዚህም ብቻ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ወደዱ። እግዚአብሔርም አዳነኝና ለታላቁም፥ ለታናሹም እየመሰከርሁ እስከ ዛሬ ደረስሁ፤ ይደረግ ዘንድ ካለው፥ ነቢያት ከተናገሩት፥ ሙሴም ከተናገረው ሌላ ያስተማርሁት የለም። ክርስቶስ እንደሚሞት፥ ከሙታን ተለይቶም አስቀድሞ እንደሚነሣ፥ ለሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ፥ ለመላውም ዓለም እንደሚያበራ።” ይህንም ስለ ራሱ ሲናገር ሀገረ ገዢው ፊስጦስ መለሰ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “ጳውሎስ ሆይ፥ ልታብድ ነውን? ብዙ ትምህርት እኮ ልብን ይነሣል” አለው። ጳውሎስም እንዲህ አለው፥ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ እውነትና የተጣራ ነገርን እናገራለሁ እንጂ ዕብደትስ የለብኝም። በፊቱ ገልጬ የምናገርለት እርሱ ራሱ ንጉሥ አግሪጳ ያውቅልኛል፤ ከዚህም የሚሳተው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ ወደ ጎን የተሰወረ አይደለምና። ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እነሆ፥ በነቢያት ቃል ታምናለህን? እንደምታምንም አውቃለሁ።” አግሪጳም ጳውሎስን፥ “አሁንስ ወደ ክርስቲያንነት ልታገባኝ ጥቂት ብቻ ቀርቶሃል” አለው። ጳውሎስም፥ “በጥቂትም ቢሆን፥ በብዙም ቢሆን አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ።”
የሐዋርያት ሥራ 26 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 26
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 26:1-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos