ሐዋርያት ሥራ 22:4-8
ሐዋርያት ሥራ 22:4-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህን መንገድ የሚከተሉትንም እስከ ሞት ድረስ እያሳደድሁ፣ ወንዶችንም ሴቶችንም አስሬ ወደ ወህኒ እጥላቸው ነበር። ይህን ተግባሬን ሊቀ ካህናቱም ሆነ ሸንጎው ሁሉ ሊመሰክሩ ይችላሉ። ከእነርሱ ደብዳቤ ተቀብዬ ደማስቆ ወዳሉት ወንድሞቻቸው በመሄድ፣ እነዚህን ሰዎች አሳስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቼ ለማስቀጣት ወደዚያ እሄድ ነበር። “ስንጓዝም እኩለ ቀን ገደማ ወደ ደማስቆ እንደ ተቃረብሁ፣ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤ እኔም ምድር ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ አልሁት። “እርሱም፣ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።
ሐዋርያት ሥራ 22:4-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህን ትምህርት የሚከተሉ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት እስከ ሞት ድረስ አሳደድኋቸው። እንዲቀጡም ከዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ወደ አሉ ወንድሞች እንድሄድ ከእነርሱ ዘንድ የሥልጣን ደብዳቤ የተቀበልኋቸው ሊቀ ካህናቱና መምህራን ሁሉ ይመሰክራሉ። “ከዚህ በኋላ ወደ ደማስቆ ስሄድ ቀትር በሆነ ጊዜ ወደ ከተማው አቅራቢያ ደርሼ ሳለሁ ድንገት ታላቅ መብረቅ ከሰማይ በእኔ ላይ አንፀባረቀ። በምድር ላይም ወደቅሁ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ቃልንም ሰማሁ። እኔም መልሼ፦ ‘አቤቱ፥ አንተ ማነህ?’ አልሁት፤ እርሱም፦ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።
ሐዋርያት ሥራ 22:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቄ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። እኔም መልሼ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ።
ሐዋርያት ሥራ 22:4-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የክርስትናን እምነት የሚከተሉትን ሁሉ እስከ ሞት የማሳድድ ሰው ነበርኩ፤ ወንዶችንና ሴቶችን እያሰርኩ ወደ ወህኒ ቤት እንዲገቡ አደርግ ነበርኩ። ይህም እውነት መሆኑን የካህናት አለቃውና የሽማግሌዎች ሸንጎ በሙሉ ይመሰክሩልኛል። እንዲያውም በደማስቆ ያሉትን እነዚህን ሰዎች አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣትና ለማስቀጣት የሚያስችለኝን በደማስቆ ወደሚገኙት ወገኖቻቸው የጻፉትን ደብዳቤ የተቀበልኩት ከእነርሱ ነው። “እኔ ወደ ደማስቆ ስሄድና ወደ ከተማው ስቀርብ እኩለ ቀን ላይ በድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ አንጸባረቀ። በዚያን ጊዜ በመሬት ላይ ወደቅኹ፤ ‘ሳውል! ሳውል! ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልኩ፤ እርሱም ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።
ሐዋርያት ሥራ 22:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። “ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቄ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። እኔም መልሼ ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ፤’ አለኝ።