ሐዋርያት ሥራ 22:1-16
ሐዋርያት ሥራ 22:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እናንተ ወንድሞችና አባቶች፥ አሁን በፊታችሁ የምናገረውን ስሙኝ።” በዕብራይስጥ ቋንቋ እንደሚነግራቸው በሰሙም ጊዜ ጸጥ ብለው አዳመጡት። ጳውሎስም እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የቂልቅያ ክፍል በምትሆን በጠርሴስ ከተማ ተወለድሁ፤ በዚችም ከተማ ከገማልያል እግር ሥር ሆኜ አደግሁ፤ የአባቶችንም ሕግ ተማርሁ፤ እናንተ ሁላችሁ ዛሬ እንደምታደርጉትም ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ነበርሁ። ይህን ትምህርት የሚከተሉ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት እስከ ሞት ድረስ አሳደድኋቸው። እንዲቀጡም ከዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ወደ አሉ ወንድሞች እንድሄድ ከእነርሱ ዘንድ የሥልጣን ደብዳቤ የተቀበልኋቸው ሊቀ ካህናቱና መምህራን ሁሉ ይመሰክራሉ። “ከዚህ በኋላ ወደ ደማስቆ ስሄድ ቀትር በሆነ ጊዜ ወደ ከተማው አቅራቢያ ደርሼ ሳለሁ ድንገት ታላቅ መብረቅ ከሰማይ በእኔ ላይ አንፀባረቀ። በምድር ላይም ወደቅሁ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ቃልንም ሰማሁ። እኔም መልሼ፦ ‘አቤቱ፥ አንተ ማነህ?’ አልሁት፤ እርሱም፦ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። አብረውኝ የነበሩትም መብረቁን አይተው ደነገጡ፤ ነገር ግን ይናገረኝ የነበረውን ቃል አልሰሙም። ‘አቤቱ፥ ጌታዬ ምን ላድርግ?’ አልሁ፤ ጌታም፦ ‘ተነሥና ወደ ደማስቆ ሂድ፤ ልታደርገው የሚገባህንም ሁሉ በዚያ ይነግሩሃል’ አለኝ። ከዚያም በኋላ ከመብረቁ ነፀብራቅ የተነሣ ዐይኔን ታወርሁ፤ አብረውኝ የነበሩትም እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። “እንደ ሕጉም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በደማስቆም የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ያመሰግኑት ነበር። ወደ እኔም መጥቶ በፊቴ ቆመና፦ ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ’ አለ፤ ያንጊዜም ወደ እርሱ አየሁ። እንዲህም አለኝ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅና ጽድቁንም ታይ ዘንድ፥ ቃሉንም ከአንደበቱ ትሰማ ዘንድ መረጠህ። በሕዝብም ሁሉ ዘንድ ባየኸውና በሰማኸው ምስክር ትሆነዋለህ። አሁንም የምታደርገውን ልንገርህ፦ ተነሥ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’
ሐዋርያት ሥራ 22:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አሁን የማቀርብላችሁን የመከላከያ መልሴን ስሙኝ።” እነርሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ፣ ከፊት ይልቅ ጸጥ አሉ። ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ “እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ የተወለድሁ አይሁዳዊ ስሆን፣ ያደግሁት ግን በዚህ ከተማ ነው። የአባቶቻችንን ሕግ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ በሚገባ ተምሬአለሁ፤ ዛሬ እናንተ እንዲህ የምትቀኑለትን ያህል እኔም ለእግዚአብሔር እቀና ነበር። ይህን መንገድ የሚከተሉትንም እስከ ሞት ድረስ እያሳደድሁ፣ ወንዶችንም ሴቶችንም አስሬ ወደ ወህኒ እጥላቸው ነበር። ይህን ተግባሬን ሊቀ ካህናቱም ሆነ ሸንጎው ሁሉ ሊመሰክሩ ይችላሉ። ከእነርሱ ደብዳቤ ተቀብዬ ደማስቆ ወዳሉት ወንድሞቻቸው በመሄድ፣ እነዚህን ሰዎች አሳስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቼ ለማስቀጣት ወደዚያ እሄድ ነበር። “ስንጓዝም እኩለ ቀን ገደማ ወደ ደማስቆ እንደ ተቃረብሁ፣ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤ እኔም ምድር ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም፣ ‘ሳውል! ሳውል! ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ አልሁት። “እርሱም፣ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። ከእኔ ጋራ የነበሩትም ብርሃኑን አዩ፤ ነገር ግን የሚናገረኝን የርሱን ድምፅ በትክክል አልሰሙም። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ምን ላድርግ?’ አልሁት። “ጌታም፣ ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህ ሁሉ ይነገርሃል’ አለኝ። ከብርሃኑም ጸዳል የተነሣ ዐይኔ ስለ ታወረ፣ ከእኔ ጋራ የነበሩት እጄን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አደረሱኝ። “ከዚያም ሐናንያ የተባለ ሰው ሊያየኝ ወደ እኔ መጣ፤ እርሱም ሕግን በጥንቃቄ የሚጠብቅና በዚያ በሚኖሩ አይሁድ ሁሉ የተመሰከረለት ሰው ነበረ። በአጠገቤም ቆሞ፣ ‘ወንድም ሳውል ሆይ፤ ዐይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ፤ እኔም በዚያችው ቅጽበት አየሁት። “እርሱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ቃሉን ከአንደበቱ እንድትሰማ መርጦሃል፤ ስላየኸውና ስለ ሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆነዋለህና። ታዲያ፣ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥተህ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’
ሐዋርያት ሥራ 22:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ ወንድሞች አባቶችም፥ አሁን ለእናንተ ንገሬን ስገልጥ ስሙኝ። በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ፦ እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቄ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። እኔም መልሼ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ። ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፥ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም። ጌታ ሆይ፥ ምን ላድርግ? አልሁት። ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል አለኝ። ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ፦ ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ። እርሱም አለኝ፦ የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና። አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።
ሐዋርያት ሥራ 22:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ወንድሞቼና አባቶቼ ሆይ! እነሆ፥ አሁን የማቀርብላችሁን መከላከያ ስሙኝ!” በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ በይበልጥ ጸጥ አሉ፤ ጳውሎስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ ያደግኹት ግን በዚህች በኢየሩሳሌም ከተማ ነው። አስተማሪዬም ገማልያል ነበር፤ የአባቶችን ሕግ ጠንቅቄ የተማርኩና ልክ ዛሬ እናንተ እንደምታደርጉት እግዚአብሔርን በመንፈሳዊ ቅናት የማገለግል ነበርኩ። የክርስትናን እምነት የሚከተሉትን ሁሉ እስከ ሞት የማሳድድ ሰው ነበርኩ፤ ወንዶችንና ሴቶችን እያሰርኩ ወደ ወህኒ ቤት እንዲገቡ አደርግ ነበርኩ። ይህም እውነት መሆኑን የካህናት አለቃውና የሽማግሌዎች ሸንጎ በሙሉ ይመሰክሩልኛል። እንዲያውም በደማስቆ ያሉትን እነዚህን ሰዎች አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣትና ለማስቀጣት የሚያስችለኝን በደማስቆ ወደሚገኙት ወገኖቻቸው የጻፉትን ደብዳቤ የተቀበልኩት ከእነርሱ ነው። “እኔ ወደ ደማስቆ ስሄድና ወደ ከተማው ስቀርብ እኩለ ቀን ላይ በድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ አንጸባረቀ። በዚያን ጊዜ በመሬት ላይ ወደቅኹ፤ ‘ሳውል! ሳውል! ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልኩ፤ እርሱም ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ብርሃኑን አዩ እንጂ እርሱ ሲያነጋግረኝ ድምፁን አልሰሙም። እኔም ‘ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ?’ አልኩ። ጌታም ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ ልታደርገው የሚገባህ ነገር ሁሉ እዚያ ይነገርሃል’ አለኝ። ከብርሃኑ ማንጸባረቅ የተነሣ ማየት ስላልቻልኩ አብረውኝ የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ አደረሱኝ። “እዚያ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው በደማስቆ በሚኖሩት አይሁድ ሁሉ የተመሰገነ፥ ሕግ አክባሪና መንፈሳዊ ሰው ነበረ። እርሱ ወደ እኔ መጥቶ አጠገቤ ቆመና ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ! ዐይንህ እንደገና ይይልህ!’ አለኝ፤ በዚያኑ ቅጽበት ዐይኔ አየ፤ እርሱንም ተመለከትኩት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ ጻድቁን እንድታይና ድምፁንም እንድትሰማ አስቀድሞ መርጦሃል። ይህንንም ያደረገው ስላየኸውና ስለ ሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት የእርሱ ምስክር እንድትሆን ነው። ታዲያ፥ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥና የእርሱን ስም በመጥራት ተጠመቅ፤ ከኃጢአትህም ታጠብ።’
ሐዋርያት ሥራ 22:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እናንተ ወንድሞች አባቶችም! አሁን ለእናንተ ንገሬን ስገልጥ ስሙኝ።” በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ። ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። “ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቄ ‘ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። እኔም መልሼ ‘ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ፤’ አለኝ። ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፤ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም። ‘ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ?’ አልሁት። ጌታም ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል፤’ አለኝ። ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። “በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ! እይ፤’ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ። እርሱም አለኝ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል፤ ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና። አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኃጢአትህም ታጠብ።’