የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 16:16-33

ሐዋርያት ሥራ 16:16-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ለጸ​ሎት ስን​ሄ​ድም የም​ዋ​ር​ተ​ኛ​ነት መን​ፈስ ያደ​ረ​ባት አን​ዲት ልጅ አገ​ኘ​ችን፤ በጥ​ን​ቈ​ላም የም​ታ​ገ​ኘ​ውን ብዙ እጅ መንሻ ለጌ​ቶ​ችዋ ታገባ ነበር። ከዚ​ህም በኋላ ጳው​ሎ​ስ​ንና እኛን እየ​ተ​ከ​ተ​ለች፥ “እነ​ዚህ ሰዎች የል​ዑል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አገ​ል​ጋ​ዮች ናቸው፤ የሕ​ይ​ወ​ት​ንም መን​ገድ ያስ​ተ​ም​ሩ​አ​ች​ኋል” እያ​ለች ትጮኽ ነበር። ብዙ ቀንም እን​ዲሁ ታደ​ርግ ነበር፤ ጳው​ሎ​ስ​ንም አሳ​ዘ​ነ​ችው፤ መለስ ብሎም፥ “መን​ፈስ ርኩስ፥ ከእ​ር​ስዋ እን​ድ​ት​ወጣ በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ስም አዝ​ዤ​ሃ​ለሁ” አለው፤ ወዲ​ያ​ው​ኑም ተዋት። ጌቶ​ች​ዋም የም​ታ​ገ​ባ​ላ​ቸው የጥ​ቅ​ማ​ቸው ተስፋ እንደ ቀረ ባዩ ጊዜ ጳው​ሎ​ስ​ንና ሲላ​ስን ይዘው በገ​በያ እየ​ጐ​ተቱ ወደ ገዢ​ዎች ወሰ​ዱ​አ​ቸው። ወደ ገዢ​ዎ​ችም አቅ​ር​በው፥ “እነ​ዚህ ሰዎች ከተ​ማ​ች​ንን ያሸ​ብ​ሩ​ብ​ናል፤ እነ​ር​ሱም አይ​ሁድ ናቸው። እኛ የሮሜ ሰዎች ስን​ሆ​ንም ልና​ደ​ር​ገው የማ​ይ​ገ​ባ​ንን ሕግ ይና​ገ​ራሉ” አሉ። ሕዝ​ቡም ተነ​ሡ​ባ​ቸው፤ ገዢ​ዎ​ቹም ልብ​ሳ​ቸ​ውን ገፍ​ፈው በበ​ትር ይመ​ቱ​አ​ቸው ዘንድ አዘዙ። በብ​ዙም ደብ​ድ​በው አሰ​ሩ​አ​ቸው፤ የወ​ህኒ ቤቱን ዘበ​ኛም አጽ​ንቶ እን​ዲ​ጠ​ብ​ቃ​ቸው አዘ​ዙት። እር​ሱም ትእ​ዛ​ዙን ተቀ​ብሎ ወደ ውስ​ጠ​ኛው ወኅኒ ቤት አስ​ገ​ባ​ቸው፤ እግ​ራ​ቸ​ው​ንም በግ​ንድ አጣ​ብቆ ጠረ​ቃ​ቸው። በመ​ን​ፈቀ ሌሊ​ትም ጳው​ሎ​ስና ሲላስ ጸለዩ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም በዜማ አመ​ሰ​ገ​ኑት፤ እስ​ረ​ኞ​ቹም ይሰ​ሙ​አ​ቸው ነበር። ድን​ገ​ትም ታላቅ ንው​ጽ​ው​ጽታ ሆነ፤ የወ​ህኒ ቤቱ መሠ​ረ​ትም ተና​ወጠ፤ በሮ​ችም ሁሉ ያን​ጊዜ ተከ​ፈቱ፤ የሁ​ሉም እግር ብረ​ቶ​ቻ​ቸው እየ​ወ​ለቁ ወደቁ። የወ​ህኒ ቤቱ ጠባ​ቂም ከእ​ን​ቅ​ልፉ በነቃ ጊዜ በሮች ሁሉ ተከ​ፍ​ተው አየ፤ ሰይ​ፉ​ንም መዝዞ ራሱን ሊገ​ድል ወደደ፤ እስ​ረ​ኞቹ ያመ​ለ​ጡት መስ​ሎት ነበ​ርና። ጳው​ሎ​ስም፥ “በራ​ስህ ክፉ ነገር አታ​ድ​ርግ፤ ሁላ​ች​ንም ከዚህ አለን” ብሎ በታ​ላቅ ቃል ጮኸ። መብ​ራት አም​ጥ​ቶም እየ​ተ​ን​ቀ​ጠ​ቀጠ ወደ ውስጥ ሄደና ለጳ​ው​ሎ​ስና ለሲ​ላስ ወድቆ ሰገደ። ወደ ውጭም አው​ጥቶ “ጌቶች፥ እድን ዘንድ ምን ላድ​ርግ?” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ እመን፤ አን​ተና ቤተ ሰብ​ህም ሁሉ ትድ​ና​ላ​ችሁ” አሉት። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ቃል ለእ​ር​ሱና በቤቱ ላሉት ሁሉ ነገ​ሩ​አ​ቸው። ወዲ​ያ​ው​ኑም በሌ​ሊት ወስዶ ቍስ​ላ​ቸ​ውን አጠ​በ​ላ​ቸው፤ እር​ሱም በዚ​ያው ጊዜ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር ተጠ​መቀ።

ሐዋርያት ሥራ 16:16-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤ ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከእርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት። አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለ ሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው። ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤ ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም የማይገባንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።” ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፍፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው። እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር። ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኛ ሁላችን እዚሁ ስላለን፣ በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርስ!” ብሎ ጮኸ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም መብራት ለምኖ ወደ ውስጥ ዘልሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ላይ ወደቀ። ይዟቸው ከወጣ በኋላ፣ “እናንት ሰዎች፤ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው። እነርሱም፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ አንተም ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” አሉት። ከዚያም ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ተናገሩ። የወህኒ ቤት ጠባቂውም ሌሊት በዚያኑ ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን ዐጠበላቸው፤ ወዲያውም እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ ተጠመቁ።

ሐዋርያት ሥራ 16:16-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው” ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ “ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎም አቅርበው፦ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ” አሉ። ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸ። በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ። የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ “ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ፦ “ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ኣላቸው። እነርሱም፦ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” አሉት። ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤

ሐዋርያት ሥራ 16:16-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አንድ ቀን ወደ ጸሎት ቦታ ስንሄድ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በጥንቈላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ ያደረባት አንዲት አገልጋይ ልጃገረድ በመንገድ አገኘችን፤ ይህች ልጃገረድ በጥንቈላዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ትርፍ ታስገኝላቸው ነበር። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው! እነርሱ የመዳንን መንገድ ያበሥሩአችኋል!” በማለት ትጮኽ ነበር። ይህንንም ብዙ ቀን እየደጋገመች ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስ ግን ተበሳጨና ዞር ብሎ ርኩሱን መንፈስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርስዋ እንድትወጣ አዝሃለሁ!” አለው። ርኩሱም መንፈስ ወዲያውኑ ወጣ። አሳዳሪዎችዋ ጥቅም የሚያገኙበት ተስፋ እንደ ተቋረጠባቸው ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ያዙአቸው፤ እየጐተቱም ወደ አደባባይ ወሰዱአቸውና በሹሞች ፊት አቀረቡአቸው። ወደ ሮማውያን ባለሥልጣኖችም አመጡአቸውና እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ወገኖች ናቸው፤ በከተማችንም ሁከት ያስነሣሉ፤ እኛ የሮም ዜጋዎች ልንቀበለው ወይም ልናደርገው ያልተፈቀደልንን ሥርዓት ያስተምራሉ።” ሕዝቡም ሁሉ ተባብሮ በእነርሱ ላይ ተነሣ። ባለሥልጣኖችም የጳውሎስንና የሲላስን ልብስ ገፈፉና በዱላ እንዲደበደቡ አዘዙ። ብዙ ከተደበደቡም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አገቡአቸው፤ የወህኒ ቤቱም ጠባቂ በጥብቅ እንዲጠብቃቸው ታዘዘ። ጠባቂው ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፥ በወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገባቸው፤ እግሮቻቸውንም በግንድና ግንድ መካከል አጣብቆ አሰራቸው። ወደ እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ በጸሎትና በመዝሙር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎችም እስረኞች ያዳምጡአቸው ነበር። በድንገት የወህኒ ቤቱ መሠረት እስኪናጋ ድረስ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ በሮቹም ሁሉ በአንድ ጊዜ ተከፈቱ፤ የእያንዳንዱም እስረኛ ሰንሰለት ተፈታ። ጠባቂው ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ። ነገር ግን ጳውሎስ፥ “ሁላችንም እዚህ ነን! ስለዚህ በራስህ ላይ ጒዳት አታድርስ!” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጠባቂው መብራት አስመጥቶ እየሮጠ ወደ ውስጥ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ሥር በግንባሩ ተደፋ። ወደ ውጪም አወጣቸውና “ጌቶቼ ሆይ! ለመዳን ምን ማድረግ ይገባኛል?” አላቸው። እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ ትድናለህ፤ ቤተሰቦችህም ይድናሉ” አሉት። የጌታንም ቃል ለእርሱና በእርሱ ቤት ላሉትም ሁሉ ተናገሩ። በዚያኑ ሰዓት በሌሊት የወህኒ ቤቱ ጠባቂ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው፤ ወዲያውኑ እርሱና ቤተሰቡ በሙሉ ተጠመቁ።

ሐዋርያት ሥራ 16:16-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርሷ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባርያዎች ናቸው፤” ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን “ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፤” አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎም አቅርበው “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ፤” አሉ። ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፤ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸ። በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፤ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ። የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ “ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤” ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፤ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ “ጌቶች ሆይ! እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ኣላቸው። እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ፤” አሉት። ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤