የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 16:16-33

የሐዋርያት ሥራ 16:16-33 አማ05

አንድ ቀን ወደ ጸሎት ቦታ ስንሄድ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በጥንቈላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ ያደረባት አንዲት አገልጋይ ልጃገረድ በመንገድ አገኘችን፤ ይህች ልጃገረድ በጥንቈላዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ትርፍ ታስገኝላቸው ነበር። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው! እነርሱ የመዳንን መንገድ ያበሥሩአችኋል!” በማለት ትጮኽ ነበር። ይህንንም ብዙ ቀን እየደጋገመች ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስ ግን ተበሳጨና ዞር ብሎ ርኩሱን መንፈስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርስዋ እንድትወጣ አዝሃለሁ!” አለው። ርኩሱም መንፈስ ወዲያውኑ ወጣ። አሳዳሪዎችዋ ጥቅም የሚያገኙበት ተስፋ እንደ ተቋረጠባቸው ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ያዙአቸው፤ እየጐተቱም ወደ አደባባይ ወሰዱአቸውና በሹሞች ፊት አቀረቡአቸው። ወደ ሮማውያን ባለሥልጣኖችም አመጡአቸውና እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ወገኖች ናቸው፤ በከተማችንም ሁከት ያስነሣሉ፤ እኛ የሮም ዜጋዎች ልንቀበለው ወይም ልናደርገው ያልተፈቀደልንን ሥርዓት ያስተምራሉ።” ሕዝቡም ሁሉ ተባብሮ በእነርሱ ላይ ተነሣ። ባለሥልጣኖችም የጳውሎስንና የሲላስን ልብስ ገፈፉና በዱላ እንዲደበደቡ አዘዙ። ብዙ ከተደበደቡም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አገቡአቸው፤ የወህኒ ቤቱም ጠባቂ በጥብቅ እንዲጠብቃቸው ታዘዘ። ጠባቂው ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፥ በወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገባቸው፤ እግሮቻቸውንም በግንድና ግንድ መካከል አጣብቆ አሰራቸው። ወደ እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ በጸሎትና በመዝሙር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎችም እስረኞች ያዳምጡአቸው ነበር። በድንገት የወህኒ ቤቱ መሠረት እስኪናጋ ድረስ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ በሮቹም ሁሉ በአንድ ጊዜ ተከፈቱ፤ የእያንዳንዱም እስረኛ ሰንሰለት ተፈታ። ጠባቂው ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ። ነገር ግን ጳውሎስ፥ “ሁላችንም እዚህ ነን! ስለዚህ በራስህ ላይ ጒዳት አታድርስ!” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጠባቂው መብራት አስመጥቶ እየሮጠ ወደ ውስጥ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ሥር በግንባሩ ተደፋ። ወደ ውጪም አወጣቸውና “ጌቶቼ ሆይ! ለመዳን ምን ማድረግ ይገባኛል?” አላቸው። እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ ትድናለህ፤ ቤተሰቦችህም ይድናሉ” አሉት። የጌታንም ቃል ለእርሱና በእርሱ ቤት ላሉትም ሁሉ ተናገሩ። በዚያኑ ሰዓት በሌሊት የወህኒ ቤቱ ጠባቂ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው፤ ወዲያውኑ እርሱና ቤተሰቡ በሙሉ ተጠመቁ።