ሐዋርያት ሥራ 10:24-33
ሐዋርያት ሥራ 10:24-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው። ጴጥሮስም እያነጋገረው ዐብሮት ሲገባ፣ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋራ እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል። ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሷል። ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤ እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፏል።’ እኔም ወዲያው ላክሁብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ እኛ ሁላችን ጌታ ያዘዘህን ስትነግረን ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት አለን።”
ሐዋርያት ሥራ 10:24-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስም፥ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ። አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፥ “የዛሬ አራት ቀን በዘጠኝ ሰዓት በዚች ሰዓት በቤቴ ስጸልይ የሚያንፀባርቅ ልብስ የለበሰ አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ ታየኝ። እንዲህም አለኝ፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ፤ ምጽዋትህም ታሰበልህ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ከተማ ላክና በባሕር አቅራቢያ ባለችው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ፤ እርሱ መጥቶ የምትድንበትን ይነግርሃል። ስለዚህም ወዲያውኑ ወደ አንተ ላክሁ፤ ወደ እኛ በመምጣትህም መልካም አደረግህ፤ አሁንም እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ ልንሰማ እነሆ፥ እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።”
ሐዋርያት ሥራ 10:24-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፦ “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ፦ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና፦ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል” አለኝ። ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።
ሐዋርያት ሥራ 10:24-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሁለተኛውም ቀን ወደ ቂሳርያ ደረሱ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ እነጴጥሮስን ይጠባበቅ ነበር። ጴጥሮስ ወደ ቤት ሲገባ ቆርኔሌዎስ ወደ እርሱ ቀረበና በእግሩ ሥር ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሥ! እኔም እንደ አንተ ሰው ነኝ!” ብሎ አስነሣው። እያነጋገረውም ወደ ውስጥ ሲገባ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ። እንዲህም አላቸው፦ “አይሁዳዊ ለሆነ ሰው ከሌላ ሕዝብ ጋር ለመተባበርና ወደ ቤቱም ለመግባት በሃይማኖታችን ሕግ እንደማይፈቀድ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ማንንም ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ እንዳልል እግዚአብሔር ገልጦልኛል። ስለዚህ በተላከብኝ ጊዜ ያለ አንዳች ተቃውሞ መጣሁ፤ እንግዲህ ለምን እንደ ጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፦ “ከአራት ቀን በፊት ልክ በዚህ ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆ፥ በድንገት አንድ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመ፤ እንዲህም አለኝ፦ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቶአል፤ ለድኾች የምታደርገውም ምጽዋት ታስቦልሃል፤ እንግዲህ ወደ ኢዮጴ መልእክተኛ ላክና ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በባሕር አጠገብ በሚገኘው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ተቀምጦአል፤’ ስለዚህ ወዲያውኑ መልእክተኞች ወደ አንተ ላክሁ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል፤ እንግዲህ እግዚአብሔር እንድትናገር ያዘዘህን ሁሉ ለመስማት እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት እዚህ ተሰብስበናል።”
ሐዋርያት ሥራ 10:24-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ፤” ብሎ አስነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ‘ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው’ እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ” አላቸው። ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው “በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቁርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ በእንግድነት ተቀምጦአል፤’ አለኝ። ስለዚህ ያንጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።”